Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮ- ሩሲያ፦ ከትናንት እስከ ዛሬ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በሩሲያ እና በአፍሪካ አህጉር መካከል ያለው ሁለንተናዊ ግንኙነት በጋራ ጥቅም፣ በእኩልነት እና ሉዓላዊነት መርሆች ላይ ተመስርቶ ወደ አዲስ ስትራቴጂካዊ አጋርነት እየተሸጋገረ ነው።

ዛሬ እና ነገ በሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ በሚካሄደው ሦስተኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባዔ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ የበርካታ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እንደሚታደሙ ይጠበቃል።

በዚህ ታሪካዊ ጉባዔ ላይ ከአፍሪካ መሪዎች በተጨማሪ የየሀገራቱ የንግድ ተቋማትና ኩባንያዎች ተሳታፊ ይሆናሉ።

የጉባዔው ዋና ዓላማ ምንድን ነው?

የጉባዔው ዋና ዓላማ፤ በሩስያ እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ተጨባጭና ዘላቂ ስትራቴጂካዊ አጋርነት በማሸጋገር የየሀገራቱን ሉዓላዊነት፣ የኢኮኖሚ ጥንካሬ እና የቴክኖሎጂ ዐቅም በጋራ ማደርጀት ነው። የጉባዔው መሪ ሐሳብም “ሰላም፣ ደኅንነትና ልማት” በሚል ነው

የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ግንኙነት

የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ግንኙነት ከ125 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ጠንካራ መሠረት ያለው ነው።

በ1888 ዓ.ም በዓድዋ ጦርነት ወቅት ሩሲያ ለኢትዮጵያ የላከችው የሕክምና ቡድን እና ያደረገችው የቁሳቁስና የሞራል ድጋፍ ለሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ወዳጅነት መጀመር መሠረት የጣለ ሲሆን ፣ በሶቪየት ህብረት ዘመንም ሆነ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ መድረኮች የሀገራትን ሉዓላዊነት በማስከበር እና የኒዮ-ኮሎኒያሊዝም ጫናዎችን በመከላከል በኩል የጸና በጋራ አቋም አላቸው።

የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ፣ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ትብብር አስመልክቶ የታሪክ ተመራማሪው ሮበርት ፓትማን “The Soviet Union in the Horn of Africa: “በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንደጠቆሙት፤ ሶቪየት ህብረት ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ከፍተኛ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ድጋፍ በማድረግ በተለይም በ1969 ዓ.ም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ግዛታዊ አንድነት ለማስከበር ዓይነተኛ ሚና ተጫውታለች።

የተከናወኑ ሥራዎች

ሩሲያ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ ሊጣሉ የነበሩ ማዕቀቦችን በመቃወም የሀገራቸን ዲፕሎማሲያዊ ጥበቃ ሆናለች፤ ኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS Plus) አባል እንድትሆንም ከፍተኛ ድጋፍ ሰጥታለች። በተጨማሪም ለመከላከያ ሠራዊቱ የወታደራዊ የቴክኒክ ድጋፍና ለባህር ኃይል ግንባታ ሥልጠናዎችን በመስጠት ላይ ትገኛለች።

በሌላ በኩል የግብርና ማሽነሪዎችንና የነዳጅ መሣሪያዎችን ለኢትዮጵያ የምታቀርብ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በበኩሏ ቡና፣ የቪየና አበባና ጨርቃጨርቅ ወደ ሩሲያ በመላክ ላይ ትገኛለች።

የሩሲያው ‘ሮሳቶም’ (Rosatom) ኩባንያ በኢትዮጵያ የሰላማዊ ኑክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባትና የሲቪል ኑክሌር መተግበሪያዎችን ለማስፋፋት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የተፈራረመውን ስምምነት ወደ ትግበራ አሸጋግሯል።

ሩሲያ በህዋ ሳይንስ፣ በሰው-ሠራሽ አስተውሎት (AI)፣ በሳይበር ደህንነትና ዲጂታል ቢዝነስ ልምዷን ለማካፈል ዝግጁነቷን አሳይታለች። በተጨማሪም በጤና አጠባበቅ፣ በባሕል ልውውጥ፣ በሙዚየም አስተዳደር እና በሳይንሳዊ ምርምሮች የጋራ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

የተገኙ ውጤቶች

ሩስያ የኢትዮጵያ ባላት ውግንና በክፉ ቀናት ሁሉ የሀገራችን ሉዓላዊነት እንዳይደፈር ድጋፍ አድርጋለች።

በቅርቡም የብሪክስ ጥምረት (BRICS Plus) አባል ለመሆን ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ በማድረግ ስትራቴጂያዊ አጋርነቷን አሳይታለች። ኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS Plus) አባል እንድትሆን ሩሲያ ላደረገችው የማይናወጥ ድጋፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ምስጋና መቅረባቸውም ይታወሳል።

የሁለቱ ሀገራት ዓመታዊ የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥ በሦስት እጥፍ (በ300%) አድጎ 435 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ደርሷል።

በትምህርትና ሥልጠና ረገድ እስካሁን ከ20 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በሩሲያ ነፃ የትምህርት፣ የሕክምና እና የሙያ ሥልጠና ዕድሎች ተጠቃሚ ሆነዋል።

ከጉባዔው ምን ይጠበቃል?

በጉባዔው በሚፈረሙ የንግድና ቴክኖሎጂ ውሎች መሠረት ኢትዮጵያ የሰላማዊ ኑክሌር ኃይል ግንባታ ሂደቷን ለማፈጠን የሚያስችል ምቹ ሁኔታ የሚፈጠር ሲሆን፣ በህዋ ሳይንስና ዲጂታል መሠረተ-ልማት የቴክኖሎጂ ሽግግር ድጋፍ ታገኛለች ተብሎ ይጠበቃል ።

በተጨማሪም አዲሱ የሩስያ-አፍሪካ የድርጊት መርሃ-ግብር (2027–2029) ሲጸድቅ፣ የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች (ቡና፣ አበባ፣ ጥራጥሬ) ያለ ታሪፍ ገደብ ወደ ሩሲያ ገበያ የሚገቡበት እድል ይሰፋል።
ከሩሲያ የሚመጣውን የማዳበሪያና የግብርና ግብአቶች አቅርቦት ዋጋ በመቀነስና መጠኑን በመጨመር ሀገራዊ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ያስችላል።

በጉባዔው በጋራ በሚጸድቀው የፖለቲካ የአቋም መግለጫ መሠረት ደግሞ፣ ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን ዓለም አቀፍ ሥርዓት (BRICS+ እና ተመድ) ውስጥ አህጉራዊና ሀገራዊ ሉዓላዊቷን የሚያስከብር ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስኬት ታገኛለች ተብሎ ይጠበቃል።

በአሰፋ አሕመድ

Exit mobile version