አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ25 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል አለ የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ።
የቢሮ ኃላፊ አሰለፈች መብራቱ እንደገለጹት ፥ በሩብ ዓመቱ ለ11 ሺህ ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ዕቅዱን በእጅጉ በማብለጥ 25 ሺህ 374 ወጣቶችን የስራ ዕድሎች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
ከዚሁ ጎን ለጎን ወጣቶችን በኢኮኖሚ ለማጠናከር በተደረገው እንቅስቃሴ 4 ሺህ 600 ወጣቶችን የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ፣ ከ6 ሺህ 900 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የብድር አገልግሎት ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል።
አክለውም በክልሉ የሴቶችና ህፃናትን መብትና ደህንነት ከመጠበቅ ባሻገር ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በሩብ ዓመቱ ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመዋል።
የሴቶችና ህፃናት መብትና ደህንነት ማስጠበቅ የአንድ አካል ብቻ ኃላፊነት አለመሆኑንና የተጣለውን ግብ ለማሳካት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራርና ርብርብ ወሳኝ መሆኑንም አሳስበዋል።
በተስፋዬ ምሬሳ

