አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመከላከያ ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ ከአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኤምስበርገር ጋር ተወያይተዋል፡፡
ውይይቱ በወቅታዊ የደህንነት፣ የሰላም ግንባታ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
ጦርነቱ በኢትዮጵያ ፍላጎት የተነሳ ባይሆንም፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ግን የሕዝብ ደህንነትን ባከበረ መልኩ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ጥቃቱን በብቃት መመከት መቻሉን ሚኒስትሩ በውይይቱ አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል የባለአደራ አሥተዳደር ተቋቁሞ ከስድስት ወራት በኋላ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድና ክልሉ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት ሁኔታ እየተመቻቸ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በተጨማሪም መንግሥት የቀድሞ ተዋጊዎችን በDDR ፕሮግራም ወደ ኅብረተሰቡ ለማቀላቀል እያከናወነ ላለው ተግባር የአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚህ ጎን ለጎንም የክልሉን ሕዝብ ሁለንተናዊ የልማት ፍላጎት ለማሟላት፣ ከግጭት በኋላ ማኅበራዊ ተቋማትን ለማነቃቃት፣ የልማት እንቅስቃሴዎችን ለማስጀመር እና ማኅበረሰቡን ወደ መደበኛ ሕይወት ለመመለስ በመንግሥት የሚደረጉትን ጥረቶች የአውሮፓ ኅብረት እንዲያግዝ ጠይቀዋል።
የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኤምስበርገር በተደረገላቸው ገለጻ መደሰታቸውን ገልጸዋል። በትግራይ ክልል እየተከናወኑ ያሉ ሂደቶችን በቅርበት እየተከታተሉ መሆናቸውንና ቀደም ሲል ከነበራቸው መረጃ በላይ ግልጽ ግንዛቤ ማግኘት መቻላቸውንም ተናግረዋል።
አምባሳደሯ የአውሮፓ ኅብረት ለመንግሥት የሰላም እና የመልሶ ማቋቋም ጥረቶች አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ማረጋገጣቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።

