አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃዱ ቀደም ሲል የተሰረዘው “ድምጺ ወያነ ትግራይ ሬዲዮና ቴሌቪዥን አገልግሎት”፣ “ማእዶት ብሮድካስቲንግ አገልግሎት” በሚል አዲስ ስያሜ የብሮድካስት ፈቃድ ተሰጥቶታል አለ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን።
ባለሥልጣኑ በአዋጅ ቁጥር 1238/2013 በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት ባደረገው ክትትልና ቁጥጥር፣ ጣቢያው
ከመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ጋር የሚቃረኑ ይዘቶችን በሕገ ወጥ መንገድ ሲያሰራጭ በመገኘቱ ፈቃዱ መሰረዙ ይታወሳል።
ሆኖም በትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር፤ ቀደም ሲል ድምጺ ወያነ ትግራይ ሬድዮና ቴሌቪዥን በሚል የሬድዮና ቴሌቪዥን አገልግሎት ሲሰጥ የነበረዉ ጣቢያ የጦርነት መሳሪያ ሆኖ በማገልገሉ ምክንያት ፈቃዱ እንደተሰረዘ አስታዉሶ፣ ይሁንና አሁን ክልሉን የሚመራዉ የባለአደራ አስተዳዳር የክልሉን ሰላምና መረጋጋት በማረጋገጥ እንዲሁም የሕዝብ ድምፅ በመሆን አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የስያሜ ለዉጥ በማድረግ ማእዶት ብሮድካስቲንግ አገልግሎት በሚል በአዲስ ስያሜ ተቀይሮ ፈቃድ እንዲሰጠዉ ያቀረበውን ጥያቄ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ከመገናኛ ብዙሃን አዋጅ አንፃር በመመርመር ጥያቄው ተገቢነት ያለው መሆኑን በማመን ተቀብሎታል፡፡
ስለሆነም ባለሥልጣኑ ማእዶት ብሮድካስቲንግ አገልግሎት በሚል አዲስ የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ የሰጠ መሆኑን እያሳወቅን፤ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ለብሮድካስት አገልግሎቱ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ባለሥልጣኑ ጥሪ አቅርቧል።

