Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከህዝብ ጋር መወያየት የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት አይነተኛ መንገድ ነው – መሳይ ኃይሉ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ከህዝብ ጋር ተቀራርቦ መወያየት የምንፈልጋትን የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት አይነተኛ መንገድ ነው አሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር መሳይ ኃይሉ (ዶ/ር)።
ርዕሰ መስተዳድሩ በማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ከሚገኙ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ከተውጣጡ የሕዝብ ተወካዮች ጋር በይርጋለም ከተማ የውይይት መድረክ እያካሄዱ ይገኛሉ።
መሳይ ኃይሉ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ሲዳማ ከጥንት ጀምሮ የመደማመጥ፣ የመከባበርና የመግባባት ባህል ያለው ሕዝብ ነው።
በመሆኑም እነዚህን እሴቶች በማጠናከር በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን ትብብር ማሳደግ ለክልሉ ልማት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም ማዕከላዊ ሲዳማ ዞንና ይርጋለም ከተማ በጤና አገልግሎት፣ በተፈጥሮ ፀጋዎች፣ በወንዞችና በፍል ውሃ የታደሉ አካባቢዎች በመሆናቸውን ገልጸው እነዚህን ሀብቶች በተቀናጀ መንገድ በመጠቀም እና ከሕዝቡ ጋር በመወያየት ወደ ምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚነት መቀየር እንደሚቻል አመልክተዋል።
የማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቴድሮስ ገቢባ በበኩላቸው÷ ሕዝቡ የሚያነሳቸውን የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች በየደረጃው ምላሽ በመስጠት ለመፍታት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የሕዝብና የመንግሥት ውይይት የልማት ፍላጎቶችን ለመለየት፣ የሕዝብን ተሳትፎ ለማሳደግና አካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ሀብቶች በጋራ ጥረት ወደ ዘላቂ ልማት ለመቀየር ወሳኝ ሚና እንደሚጫወትም አስረድተዋል።
በጥላሁን ይልማ
Exit mobile version