Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የቀጣናው ሀገራት የባህር ላይ ደህንነት እና የነፍስ አድን ትብብር ፎረም ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር በመተባበር ሲያካሂደው የቆየው የቀጣናው ሀገራት የባህር ላይ ደህንነት ፎረም ተጠናቅቋል።

በፎረሙ ላይ የየመን፣ የኦማን፣ የጂቡቲ፣ የሱማሌላንድ እና የፑንትላንድ የባህር ኃይል አዛዦች ተሳትፈዋል።

በውይይቱ በቀጠናው ሀገራት መካከል ያለውን የባህር ላይ የነፍስ አድን እና የደህንነት ሥራ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የልምድ ልውውጥ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ኮሞዶር ጀማል ቱፊሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፥ ቀጣናዎችን የመለየት፣ የጋራ ዘመቻ ልምምድ ለማድረግና ድንበር ተሻጋሪ መረጃዎችን በመለዋወጥ የቀጠናውን የባህር ላይ ደህንነት ለመጠበቅ ተጨባጭ አቅም መፍጠር ተችሏል።

ተሳታፊዎችም ወርክሾፑ ያስገኘውን ልምድ ወደ ተግባር በመቀየር በቀጠናው ውጤታማና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ሥራ እንዲሠሩ እምነት መጣሉን ገልጸዋል።

በመፈለግ እና ነፍስ አድን ፕሮጀክት ባለሙያ ሬር አድሚራል ኬኔት ኒጀንስ እና የጂቡቲ ኮድ ኦፍ ኮንዳክት ማናጀር ማስተር ኩራጃ ሚሺኒ በበኩላቸው፣ በቀጣናው የሚከሰቱ ሠጋቶችን ለመከላከል የመረጃ ልውውጥና ሚዛናዊ ውሳኔዎችን ማስተላለፍ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ላሳየው ተነሳሽነት ምስጋና አቅርበው፣ በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ጽኑ ቁርጠኝነት ማረጋገጣቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ባህር ኃይል አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንድ ገዙ ለፎረሙ ለተሳታፊዎች ሰርተፍኬት እና ስጦታ አበርክተዋል።

Exit mobile version