አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና የሩሲያው ዓለም አቀፍ የዜና ሚዲያ አር ቲ (Russia Today) በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን አዲስ የትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የተፈራረሙት የRT ምክትል ዋና ሥራ አሰፈጻሚ ካሪና መሊክያን እና የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን አቻቸዉ አቶ ዳዊት መስፍን ናቸዉ።
ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት ቀደም ሲል የነበራቸውን የጋራ አጋርነት በማደስ፣ በይበልጥ በሰፊውና በጥልቀት በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸው ነው።
የሩሲያው አር ቲ (Russia Today ) ዋና መስሪያ ቤቱ በሞስኮ የሚኝ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ የሚዲያ ተቋማት አንዱ ነው።
ተቋሙ በአስር ቋንቋዎች (እንግሊዝኛ፣ ዓረብኛ፣ ስፓኒሽ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛ፣ ሰርቢያኛ፣ ቻይንኛ፣ ሂንዲ፣ ፖርቱጋልኛ እና ሩሲያኛ) የሚያቀርብ ዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን ዜና አውታር ነው።
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና አር ቲ ከዚህ ቀደም ከብሪክስ (BRICS) ጋር በተያያዙና በሌሎች ሁነቶች ላይ በጋራ ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን፣ አሁን ባደሱት ስምምነት ደግሞ በትብብር መስካቸው ላይ አዳዲስ ዘርፎችን አካትተዋል።
በዚህም መሠረት የሁለቱን ሀገራት ልማት፣ የጤና ዘርፍ እንቅስቃሴዎችና ሀገራዊ ጉዳዮችን በሚመለከት የዜና እና ይዘቶች ልውውጥ ማድረግን፣ በቴክኖሎጂና በዲጂታል ሚዲያ አሰራር ልምድ መለዋወጥን እንዲሁም የሚዲያ ባለሙያዎችን አቅም በጋራ መገንባትን ያካትታል።

