አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሠራተኞችን የጡረታ ቁጠባ በጥብቅ ቁጥጥር፣ በግልጽነት እና በጥንቃቄ በተሞላ የኢንቨስትመንት አስተዳደር እና በጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት መጠበቅ ይገባል አሉ የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)።
የአፍሪካ የመጀመሪያው “የማህበራዊ ዋስትና ሥርዓቶችን ማቀናጀት ለአፍሪካ የመሠረተ ልማት እና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው የአፍሪካ ማህበራዊ ዋስትና ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የአፍሪካ የጡረታ እና የማህበራዊ ዋስትና ተቋማት ወሳኝ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ለመደገፍና ዘላቂ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽንን እውን ለማድረግ ረጅም ጊዜ የሚቆዩ ሀገር በቀል ሀብቶችን በማንቀሳቀስ ረገድ የሚጫወቱት ስትራቴጂካዊ ሚና ከፍተኛ ነው።
የአፍሪካ ተቋማት እንደ ኃይል፣ ትራንስፖርት፣ መኖሪያ ቤት እና ዲጂታል መሠረተ ልማት ባሉ ወሳኝ ዘርፎች ላይ በጋራ ኢንቨስት የማድረግ ትልቅ አቅም እንዳላቸውም ጠቁመዋል።
ድንበር ተሻጋሪ ኢንቨስትመንቶችን በኃላፊነት ስሜት ለማሳለጥ የቁጥጥር እና ትብብር ሥራዎች እንዲጠናከሩ እና የኢንቨስትመንት ማዕቀፎችን ማቀናጀት እንደሚገባም አሳስበዋል።
መንግሥታት፣ ተቆጣጣሪ አካላት፣ የጡረታ ተቋማት እና የልማት አጋሮች ከውይይት ባለፈ የማህበራዊ ዋስትና ሥርዓቶችን ወደሚያጠናክሩና የአፍሪካን የኢኮኖሚ እድገት ወደሚያፋጥኑ ተጨባጭ ተግባራት ሊሸጋገሩ ይገባል ብለዋል፡፡
በእመቤት ሲሳይ

