አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በምግብ፣ በኃይል እና በእውቀት ላይ ኢንቨስት እያደረገች ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በሞስኮ እየተካሄደ ባለው 3ኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር) በምግብ ረገድ ቀዳሚ ዓላማችን ሕዝባችንን መመገብ እና ለዘላቂ ብልጽግና የሚሆን የግብርና ኢኮኖሚ መገንባት ነው ብለዋል።
በዚህም ከሩሲያ ጋር የሚደረግ ትብብር በግብርና ማሽኖች እና የምንሰበስበውን ምርት በስፋት የሚያቀነባብሩ ኢንዱስትሪዎች አማካኝነት ይህንን ግብ ማሳካት ተችሏል ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሩሲያ ጋር በመተባበር ከዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ የደኅንነት ደረጃዎች ጋር የተጣጣመ የመጀመሪያውን የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ለመገንባት እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ይህም በሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ላይ የተመሠረተውን የኢትዮጵያን የኃይል ማመንጫ ስብጥር እንደሚያሰፋው አስረድተዋል።
የኑክሌር ሳይንስ ከዚህ የላቀ ጠቀሜታ እንዳለው የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር) የምግብ ብክነትን መቀነስ እና ካንሰርን ለማከም እንደሚረዳ ጠቁመዋል።
አንድ አፍሪካዊ ተመራማሪ በሕዝባችን ቋንቋ መሣሪያዎችን መፍጠር መቻል አለበት፤ ተቋሞቻችንም እነዚህ መሣሪያዎች መረጃዎቻችንን እንዴት እንደሚጠቀሙበት መወሰን አለባቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በቴዎድሮስ ሳህለ

