በሩሲያ ታሪክ ውስጥ በጣም ታዋቂው አፍሪካዊ ግለሰብ፣ የታላቁ ሩሲያዊ ገጣሚ አሌክሳንደር ፑሽኪን ቅድመ-አያት አብራም ጋኒባል (Abram Gannibal) ነው።
አፍሪካዊው አብራም ጋኒባል በ18ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በታላቁ ጴጥሮስ ቤተ-መንግሥት ገባ፡፡ ንጉሡም የክርስትና አባቱ ሆነ፤ ለትምህርትም ወደ ፈረንሳይ ላከው።
ጋኒባል የወታደራዊ ስልጠና ወስዶ ኢንጂነር በመሆን፣ በመጨረሻም እስከ ጄኔራልነት ማዕረግ ደረሰ። የታሪክ ተመራማሪዎች የትውልድ ቦታውን በተመለከተ አሁንም ይከራከራሉ፤ ጋኒባል ኢትዮጵያዊ (ኤርትራዊ) ነው ወይስ ካሜሮናዊ የሚል ክርክር አለ።
የሆነ ሆኖ፣ ሩሲያውያን ስለ አፍሪካ የነበራቸው ዕውቀት ለረጅም ጊዜ የተወሰነ ነበር። የአፍሪካ ዕውቀታቸው በዋናነት በመጻሕፍት እና በጎብኚዎች ዘገባዎች የተቃኘ ነበር። ቀስ በቀስ የሩሲያ ምሁራን የአፍሪካን ጂኦግራፊ እና ታሪክ ማጥናት ያዙ። በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ለአፍሪካ የነበረው ፍላጎት የበለጠ ተግባራዊ ቅርጽ መያዝ ጀመረ። የሩሲያ ነጋዴዎች ወደ ሰሜን አፍሪካ ወደቦች እየሄዱ ይገበያዩ ነበር፤ ከግብጽም ጋር ይነጉዱ ነበር።
ሆኖም ኒኮላይ አሺኖቭ (Nikolay Ashinov) ወደ አፍሪካ ያደረገው ጉዞ የተለየ ነበር። አሺኖቭ ራሱን «የነጻ ኮሳኮች መሪ» ብሎ ይጠራ ነበር።
ከእርሱ ጋር ተመሳሳይ አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎች ይዞ በ1889 (እ.ኤ.አ.) በአሁኗ ጅቡቲ ዳርቻ ሠፈረ። አካባቢውንም «ኒው ሞስኮ» (አዲሲቷ ሞስኮ) በሚል ስያሜ የሚጠራውን የሩሲያ ሰፈራ መመሥረቱን አወጀ። በዚህ ቦታ የሩሲያን ሰንደቅ ዓላማ አውለበለበ።
ይሁንና ቦታው በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ሥር የሚታደር በመሆኑ ነገሩ ሲታወቅ፣ የፈረንሳይ ወታደራዊ ኃይሎች ሰፋሪዎቹ ምሽጉን ለቀው እንዲወጡ አዘዙ።
ኒኮላይ አሺኖቭ ለቅቆ ለመውጣት ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ አካባቢውን በመሣሪያ በመደብደብ አባላቱን በቁጥጥር ሥር አዋሉ። በኒኮላይ አሺኖቭ ተነሳሽነት (Initiative) ያልተደሰተውና ያልደገፈው የሩሲያ መንግሥት ከነገሩ ራሱን አራቀ። ይህም በአፍሪካ ውስጥ የሩሲያን ህልውና ለመመስረት ከተደረጉት በጣም ያልተለመዱ ሙከራዎች አንዱ ሆኖ አበቃ።
ይሁን እንጂ ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር የነበራት ግንኙነት በጣም የተሻለ ነበር። ኢትዮጵያ በአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት እንቅስቃሴ ወቅት ነጻነቷን ጠብቃ መቆየት የቻለች የአፍሪካ ሀገር ነበረች። ሩሲያ እና ኢትዮጵያ የክርስትና እምነትን የሚጋሩ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ ሩሲያን በግዛታቸው ላይ አደጋ የመፍጠር ፍላጎት የሌላት እውነተኛ አጋር አድርገው ይመለከቷት ነበር።
ከንጉሥ ምኒልክ ጋር የመጀመሪያውን የግል ግንኙነት የመሠረተው ሩሲያዊ ወታደራዊ መኮንን ቪክቶር ማሽኮቭ (Viktor Mashkov) ነበር። ቪክቶር ማሽኮቭ በ1889 ወደ ኢትዮጵያ በመጓዝ (በመደበኛነት የ«ኖቮዬ ቭሬምያ» ጋዜጣ ዘጋቢ በመሆን) ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ለመገናኘት ቻለ። ማሽኮቭ ወደ ሴንት ፒተርስበርግ ሲመለስ ከኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዳግማዊ ምኒልክ ለሩሲያዊው ዳግማዊ አሌክሳንደር የተላከ የግል ደብዳቤ እና የክብር መሣሪያዎችን ጨምሮ በርካታ ስጦታዎችን ይዞ ተመለሰ። በኋላም ከሩሲያው ንጉሥ ምላሽ ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ። እነዚህ ጉብኝቶች በ1898 በሁለቱ ሀገራት መካከል ኦፊሴላዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዲመሠረት መሰረት ጥለዋል።
ትብብሩ ከዲፕሎማሲ ባሻገር ወደ ወዳጅነት በፍጥነት ተስፋፋ። የኢትዮጵያ ሠራዊት ጣሊያኖችን በ1896 በዓድዋ ጦርነት ካሸነፈ በኋላ፣ የሩሲያ ቀይ መስቀል ማህበር የሕክምና ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ገባ። ዳግማዊ ምኒልክ በሩሲያ ሐኪሞች በጣም ተደንቀው ነበር።
የሩሲያው ዲፕሎማት ፒዮትር ቭላሶቭ የጻፈው አንድ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ ንጉሠ ነገሥቱ በ1898 የሆስፒታል ክፍሎችን በጎበኙበት ወቅት፣ ሆስፒታሉን መመልከት ብቻ ሳይሆን የሆስፒታል ጋውን ለብሰው፣ በቀዶ ሕክምና ላይ ተገኝተው፣ ሕመምተኞችን ጠይቀው እና የሕክምና መሣሪያዎችን በአንክሮ መርምረዋል። በጤና ጥበቃ ዘርፍ የተደረገው የሩሲያ እና የኢትዮጵያ አጋርነት በጣም ዘላቂ ከሆኑት ግንኙነቶች አንዱ ሆነ።
የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በሩሲያ የነበራቸው ታሪክ ብዙም አይታወቅም። በ1897 ዳግማዊ ምኒልክ ለዳግማዊ ኒኮላስ ጥያቄ በማቅረብ ጥቂት ወጣት ኢትዮጵያውያን በሩሲያ እንዲማሩ ጠየቁ። የሩሲያው ንጉሠ ነገሥት ተስማምቶ ዕድሜያቸው ከ17 እስከ 20 የሆኑ አምስት ወጣቶች ወደ ሩሲያ ተጓዙ። እነሱም ህክምና እና ልዩ ልዩ ሙያዎችን ተማረው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ታስቦ ነበር። ሆኖም የሩሲያ የትምህርት ስርዓት ከአፍሪካውያን ተማሪዎች ፍላጎት ጋር የተጣጣመ አልነበረም።
ለምሳሌ ያህል፣ ሁለቱ ወጣቶች ከ12 እስከ 15 ዓመት የሆኑ ህጻናትን ወደሚቀበል የሙያ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ተጠብቆ ነበር። አዲሶቹ ተማሪዎች ዕድሜያቸው ከፍ ያለ እና ሩሲያኛ የማይናገሩ በመሆናቸው፣ ልዩ የቋንቋ ትምህርት ያስፈልጋቸው ነበር፤ ይህም የበጀት ጥያቄን አስነሳ።
በኤፕሪል 1898 የፋይናንስ ሚኒስትሩ ሴርጌይ ቪቴ ለዳግማዊ ኒኮላስ አቤቱታ በማቅረብ፤ ለተማሪዎቹ ትምህርት በዓመት 250 ሩብልስ እና ለአስተማሪያቸው 1 ሺህ 200 ሩብልስ ተጨማሪ በጀት እንዲመደብ ጠየቁ። የሩሲያው ንጉሠ ነገሥት ይህንን ትንሽ የአፍሪካ ተማሪዎች ወጪ በግል ሸፍኗል።
በተመሳሳይ መልኩ የባቢቼቭ ቤተሰብ ታሪክ በጣም አስደናቂ ነው። በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ኢቫን ባቢቼቭ የተባለ የሩሲያ መኮንን ወደ ኢትዮጵያ ተጓዞ በዚያው በቋሚነት ለመኖር ወሰነ። የዳግማዊ ምኒልክ ባለሟል ሆኖ፣ ኢትዮጵያዊት አግብቶ፣ በመጨረሻም የፊታውራሪነት (አዛዥ) ማዕረግ አገኘ። ልጁ ሚሽካ ባቢቼቭ (Mishka Babichev) ከአባቱ የበለጠ ታዋቂ ሆነ።
በ1920ዎቹ መገባደጃ ላይ አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን (በኋላ አፄ ኃይለ ሥላሴ) የኢትዮጵያን የአቪዬሽን ፕሮግራም መገንባት ሲጀምሩ፣ ወጣቱ ባቢቼቭ ከቀዳሚዎቹ አንዱ ሆነ። በፈረንሳይ የበረራ ስልጠና ወስዶ ከኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹ ወታደራዊ አብራሪዎች አንዱ ሆነ። በኋላም የሀገሪቱን ሲቪል አቪዬሽን በመመሥረት ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ሚሽካ ባቢቼቭ በሶቪየት ኅብረት የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ተወካይ ሆኖ ተሾሟል።
ዛሬ የሩሲያ እና አፍሪካ ግንኙነት ከመደበኛ ስብሰባዎች እና ከኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በላይ ያካተተ ነው። በአሁኑ ወቅት ወደ 35 ሺህ የሚጠጉ አፍሪካውያን ተማሪዎች በሩሲያ ዩኒቨርሲቲዎች ተመዝግበው የሚማሩ ሲሆን፣ በልዩ ልዩ የሩሲያ ከተሞች አፍሪካውያን በንግድ፣ በአገልግሎት እና ዕቃ በማድረስ (ዴሊቨሪ) ዘርፎች ሲሠሩ ማየት የተለመደ እየሆነ መጥቷል።
በሌላ በኩል ወደ አፍሪካ ሀገራት የሚጓዙ ሩሲያውያን ቁጥር ቀስ በቀስ እየጨመረ ነው። እነዚህ ዕለታዊ ግንኙነቶች ለአዳዲስ ወዳጅነቶች፣ የቤተሰብ ትስስሮች እና ለሁለቱም ሙያዊ እና የግል ግንኙነቶች መሰረት እየጣሉ ነው። ወደፊት እነዚህ ታሪኮች በኢትዮጵያ እንደነበሩት የሩሲያ ተጓዦች ጀብዱዎች ወይም በሶቪየት ኅብረት እንደነበሩት የአፍሪካ ተማሪዎች ልምዶች ማራኪ ሆነው ሊነበቡ ይችላሉ።
(ፓቬል ቪቮቭ / Pavel Lvov ኦክቶበር 28, 2026 በራሺያ ቱደይ «From Pushkin’s ancestor to Mandela’s envoys: The untold story of Russia-Africa ties» በሚል ርዕስ ከጻፉት መጣጥፍ የተወሰደ)
በተፈሪ መኮንን

