አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ቀይ ባህር በዓለም አቀፍ የውሃ አካላት መካከል ልዩ እና ስልታዊ ስፍራ የሚይዝ ተፈጥሮ ነው።
ባህሩ ከተለመደው የባህር ውቅያኖስ ባህሪ ይልቅ በርካታ ተፈጥሯዊ ምስጢራትን በውስጡ ይዟል። ቀይ ባህር በውሃው ንጹህነት እና በሰማያዊነቱ የሚታወቅ ቢሆንም “ቀይ” የሚለውን ስም ያገኘው ግን በየወቅቱ በውሃው ላይ በሚፈነዱ Trichodesmium erythraeum በተባሉ አልጌዎች ምክንያት ነው።
በጥንታዊ አቅጣጫ አሰጣጥ ስርዓትም «ቀይ» የሚለው ቃል «ደቡብ»ን የሚወክል በመሆኑ፣ የስሙ አመጣጥ ከዚሁ አቀማመጥ ጋር ይያያዛል።
ከዚህም ባሻገር ቀይ ባህር ከየትኛውም ትልቅ ወንዝ ንጹህ ውሃ በቀጥታ የማይቀላቀለው በመሆኑ ከፍተኛ ጨዋማነትና ልዩ የሙቀት መጠን አለው።
ነገር ግን ከዚህ ሳይንሳዊ እና ጂኦግራፊያዊ እውነታ በስተጀርባ ቀይ ባህር ከኢትዮጵያ ሀገራዊ እጣ ፈንታ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው።
ቀይ ባህር በአፍሪካ እና የአረብ ቴክቶኒክ ፕላቶች በመራራቃቸው ምክንያት በየዓመቱ እያደገ የሚሄድ የጂኦሎጂ ስንጥቅ ነው፤ ይህ የቀይ ባህር መፈጠሪያ የሆነው ታላቁ የስምጥ ሸለቆ (Great Rift Valley) መስመር ደግሞ ቀጥታ ወደ አፍሪካ ምድር አልፎ የኢትዮጵያን ሰንሰለታማ ተራሮች፣ አፋርን እና የተፈጥሮ ሐይቆችን ያበጀ ነው።
ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጋር ያላት ትስስር በሰው ሰራሽ ድንበር የተበጀ ሳይሆን በምድር ቅርፊት አፈጣጠር የተቀረፀ አካላዊ እና ተፈጥሯዊ ገመድ ነው።
ይህ ተፈጥሯዊ የጂኦሎጂ ገመድ በታሪክ ሂደትም የኢትዮጵያ የስልጣኔና የኢኮኖሚ ደም ስር ሆኖ ቆይቷል። የጥንቱ አክሱም ሥልጣኔ በዓለም አቀፍ ደረጃ ገኖ እንዲወጣ ያስቻለው ዋናው ምሶሶ የቀይ ባህር በር የነበረው ታሪካዊው የአዱሊስ ወደብ ነው።
ኢትዮጵያ በወቅቱ ቀይ ባህርን በመጠቀም ከሮም፣ ግሪክ፣ ህንድ እና ቻይና ጋር ትነግድ፣ የባህል እና የሃይማኖት ልውውጥ ታደርግ ነበር።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ታላቅነት እና ብሔራዊ ደህንነት ለዘመናት ከዚሁ ባህር የመጠቀም እና የመቆጣጠር አቅሟ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነበር።
ሆኖም ግን በታሪክ አጋጣሚዎች፣ በተሸረበ ሴራ እና መመሳጠር ኢትዮጵያ ይህንን ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ የባህር በር መብቷን እንድታጣ ተደርጋለች።
የጂኦግራፊያዊ እውነታው እና የተፈጥሮ አፈጣጠሩ የሚያስረዳው ግን ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ተለይታ ልትኖር የማትችል ተፈጥሯዊ ባለቤት መሆኗን ነው።
ከ130 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላት በምስራቅ አፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት የምታስመዘግብ እና ከቀይ ባህር ዳርቻ በጥቂት ኪሎሜትሮች ብቻ የምትርቅ ሀገር የባህር በር ፍላጎቷ የቅንጦት ሳይሆን የስትራቴጂክ ህልውና ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ በታሪክ ሴራ እና በሰዎች መመሳጠር ያጣችውን ይህንን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብቷን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ፣ በህጋዊ ማዕቀፍ እና በጋራ የመልማት መርህ ከመመለስ የሚያግዳት አንዳች ኃይል አይኖርም።
የቀይ ባህር ተፈጥሯዊ አፈጣጠር እና ታሪካዊ እውነት እንደሚመሰክሩት ኢትዮጵያ በቀጣናው የሚኖራትን ሰላማዊ እና ፍትሃዊ የባህር በር ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የተፈጥሮን እና የታሪክን እውነት ወደ ትክክለኛው ቦታው መመለስ ነው።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በሶስና አለማየሁ

