Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ውሃ – የሥልጣኔ መሠረት፣ የልማት ምሰሶ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ውሃ ህይወት ነው፡፡ ህይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ ህልውናቸው በውሃ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ይህ የውሃን መሰረታዊ ፍላጎትነት የሚገልጽ ሀቅ ነው፡፡
ከመሰረታዊ ፍላጎት ባሻገር ግን፣ ውሃ የሰው ልጅ ሥልጣኔ የቆመበት ዋነኛ መሠረት ነው።
ናታን ስናይደር (ዶ/ር) የተባሉ ተመራማሪ÷ “ውሃ ከሁሉም ሀብቶች እጅግ መሰረታዊው ነው። ስልጣኔዎች የሚያብቡትም የሚፈራርሱትም በውሃ መኖር ወይም አለመኖር ላይ ተመስርተው ነው” ሲሉ ውሃ ለስልጣኔ አይተኬ ሚና እንዳለው ይገልጻሉ፡፡
ለዚህ ማሳያው ጥንታዊ የዓለም ስልጣኔዎች የተመሰረቱበትን ቦታ ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ የግብጽ ስልጣኔ በናይል ወንዝ ላይ፣ የሜሶፖታሚያ ስልጣኔ በትግሪስና ኤፍራጥስ ወንዞች ላይ፣ የደቡብ እስያ ስልጣኔ በኢንደስ ወንዝ፣ የቻይና ጥንታዊ ስልጣኔ በየሎው እና ያንግትዘ ወንዞች፣ የካርቴጅ እና የፎኒሺያን ስልጣኔዎች ደግሞ በሜድትራኒያን ባህር ዳርቻ ላይ መመስረታቸው ሁነኛ አስረጂ ነው፡፡
እነዚህ የውሃ አካሎች ለግብርና ሥራ መስፋፋት፣ ለህዝብ በቂ ምርት እንዲኖር፣ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲዳብርና የከተሞች ምስረታ እንዲፋጠን እንዲሁም የፖለቲካ ሥርዓቶች እንዲደራጁ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) “ውሃ የኢኮኖሚና የሰላም መሠረት እንጂ የተፈጥሮ ሀብት ብቻ አይደለም” ሲል ይገልጸዋል።
ሆኖም በአሁኑ ወቅት ከንጹህ ውሃ አጠቃቀም ማነስ፣ ከመሬት ውስጥ ውሃ ክምችት መመናመን፣ ከኢንዱስትሪና ግብርና ተረፈ ምርቶች ከሚወጡ ብካዮች፣ እንዲሁም ከካርቦን ልቀት ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፍ የውሃ ደህንነት ከፍተኛ አደጋ እንደተጋረጠበት የተለያዩ ሪፖርቶች ያመላክታሉ።
ይህ ቀውስ በተለይም በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት፣ በገጠር ነዋሪዎች፣ በሴቶችና ህፃናት ላይ የከፋ ጫና አሳድሯል። በዓለም ጤና ድርጅትና በዩኒሴፍ መረጃ መሠረት፣ በዓለም ዙሪያ 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ገደማ ሰዎች አሁንም ደህንነቱ የተጠበቀ የመጠጥ ውሃ አያገኙም።
ይህ ፍትሃዊ ያልሆነ ስርጭት ለምግብ ዋስትና እጦት፣ ለጤና ችግርና ለኢኮኖሚ መድቀቅ አበይት ምክንያት ሆኗል።
ኢትዮጵያ ይህንን ውድ ተፈጥሮአዊ ሀብቷን በመጠቀም የህዝቧን ህይወት ለማሻሻልና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገች ትገኛለች። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅና ዘርፈ ብዙ የታዳሽ ኃይል ልማት ባሻገር የውሃ ሃብቷን በአግባቡ ለመጠቀም ያስችላታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በመስኖ ልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ በተፋሰስ ልማትና በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአፈርና ውሃ ጥበቃን ለማጠናከር የተከናወኑ ስራዎች የሀገሪቱን የአየር ንብረት የመቋቋም አቅም አሳድገዋል።
ከዚህ ባሻገር ሀገራችን በታሪክ አጋጣሚ ያጣቸውን የባህር በር መልሳ ለማግኘት በቁርጠኝነት እየሰራች ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የህልውና ጥያቄ ነው በማለት ወደ ቀይ ባህር የመመለስ ወሳኝነትን አስምረውበታል፡፡
ኢትዮጵያ ይህን በዋጋ ሊተመን የማይችል የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ እና በኃላፊነት ስሜት በመጠቀም የብልፅግና ጉዞዋን ታስቀጥላለች፡፡
በቴዎድሮስ ሳህለ
Exit mobile version