አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የባህር ላይ እንቅስቃሴን ለማሳለጥ እና ችግሮች ሲያጋጥሙ ለመፍታት የቀጣናው ሀገራት አቅማቸውን አስተባብረው መስራት አለባቸው አሉ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ዋና አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ፡፡
በኢትዮጵያ ባህር ሃይል ጠቅላይ መምሪያ አዘጋጅነት የየመን፣ የኦማን፣ የጂቡቲ፣ የሶማሌላንድ እንዲሁም የፑንትላንድ ባህር ሀይል አዛዦች የተሳተፉበት ፎረም መካሄዱ ይታወሳል።
ፎረሙ በቀጣናው ሀገራት መካከል ያለውን የባህር ላይ የነፍስ አድን እና የደህንነት ስራ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የተሞክሮ ልውውጥ ተደርጎበታል።
ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ እንደሚመለስ ጠቁመው፤ ፎረሙ ከቀጣናው ሀገራት ጋር በቅርበትና በንግግር ለመስራት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
እየተጠናከረ የመጣው የኢትዮጵያ ባህር ኃይል በቀጣናዊና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ብቁና ተመራጭ እንደሆነ ገልጸው፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው ፎረምም ይህን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሆርሙዝ ወሽመጥ የገጠመው ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ሀገራትን ተፅዕኖ ውስጥ እየከተተ መሆኑን ጠቅሰው፤ የባህር ላይ ችግሮችን ለመከላከልና ለመፍታት የቀጣናው ሀገራት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ማንም አቅም አለኝ የሚል ሀገር ቢሆን የባህር ላይ እንቅስቃሴን ለማሳለጥም ሆነ ተግዳሮቶች ሲያጋጥሙ ብቻውን መፍታት አይችልም ያሉት ዋና አዛዡ÷ ችግሮችን ለመከላከል ትብብር አስፈላጊ መሆኑን አፅዕኖት ሰጥተዋል፡፡
ተዘጋጅቶ የነበረው ፎረም ዋና ዓላማም ይህንን ግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
በፎረሙ አሁን ያሉ ተጨባጭ ሁኔታዎችና ወደፊት የሚያጋጥሙ መላምቶች ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸው የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

