አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በጥቂት ዓመታት ውስጥ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያለውን የነዳጅ ተጠቃሚ አውቶቡሶችን ሙሉ በሙሉ ወደ ጋዝ እንቀይራለን አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነዳጅ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ የተለወጡ የመጀመሪያዎቹ 26 የከተማ አውቶብሶችን ሥራ ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት÷ ከጥቂት ወራት በፊት በጎዴ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የፈሳሽ ጋዝ ምርት መጀመሯን ካበሰረች በኋላ ምርቱን ለተጠቃሚዎች ለማድረስ ሰፊ የዝግጅት ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።
ጋዙ ከመሬት ውስጥ በጋዝ መልክ የሚወጣ በመሆኑ፤ ከምርት ቦታው በማውጣት፣ በማከማቸትና በማጓጓዝ ለተጠቃሚዎች ለማድረስ የተለየ መሠረተ ልማት እና የተቀናጀ ሥራ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ለዚህም ከተለመዱት የነዳጅ ማደያዎች በተለየ መልኩ የጋዝ ማከማቻና ማከፋፈያ ማዕከላትን ከመገንባት በተጨማሪ ጋዙን ለማጓጓዝ ልዩ የትራንስፖርት ሥርዓትና ተስማሚ ታንከሮችን ማዘጋጀት እንደነበረባቸው አብራርተዋል።
ከዚህ ባሻገር ቀደም ሲል በቤንዚንና በናፍታ የሚሠሩትን አውቶቡሶች ለጋዝ አጠቃቀም ምቹ ለማድረግ የሞተር ለውጥና ሌሎች የቴክኒክ ማስተካከያዎች ማድረግ ሌላው ሥራ እንደነበር ጠቁመዋል።
ለዚህም ከተለያዩ ሀገራት የጋዝ ሞተሮችን በማስመጣት ቀደም ሲል በአዲስ አበባ አንበሳ አውቶቡስ ድርጅት ሲያገለግሉ የነበሩ አውቶቡሶችን ወደ ጋዝ አጠቃቀም የመቀየር ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በዚህም እስካሁን ወደ 26 የሚጠጉ አውቶቡሶችን መቀየር መቻሉን ጠቅሰው፤ የአውቶቡሶቹን ማስተካከል፣ የጋዝ ማጓጓዣ ሥርዓቱን ማዘጋጀትና ማደያዎችን መገንባት የልምድና የቴክኒክ አቅም ገደቦች ባሉበት ሁኔታ የተከናወኑ ሥራዎች መሆናቸውን አመልክተዋል።
በቀጣዮቹ ሦስት ወራት ውስጥ ወደ 400 የሚጠጉ በተፈጥሮ ጋዝ የሚሠሩ አውቶቡሶች ይገባሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህ አውቶቡሶች እስኪገቡ ድረስም ነባር አውቶቡሶችን ወደ ጋዝ የመቀየር ሥራው እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
400ዎቹ አውቶቡሶች ወደ አገልግሎት ሲገቡ በአዲስ አበባ ከሚገኙት የአንበሳ አውቶቡሶች ውስጥ ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆኑት በተፈጥሮ ጋዝ የሚሠሩ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።
በቀጣዮቹ ዓመታትም የጋዝ አውቶቡሶችን ቁጥር በየደረጃው በማሳደግ በአዲስ አበባ በነዳጅ የሚሠሩ የከተማ አውቶቡሶችን በሙሉ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ ለመቀየር መታቀዱን አስረድተዋል።
በዮናስ ጌትነት

