አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) መጪው ጊዜ ለልጆቻችን እና ለኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪና ብሩህ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከነዳጅ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ የተለወጡ የመጀመሪያዎቹ 26 የከተማ አውቶብሶችን ሥራ ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት፤ ሀገር በአንድ ጀምበር እና በአንድ ትውልድ አትገነባም፤ ሀገር መገንባት ውስብስብ ሂደት አለው፡፡
ጋዝ እናወጣለን ብለን ጋዝ ማውጣት ችለናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) መናገር ብቻ ሳይሆን፤ የሚያጋጥሙትን ፈተናዎችን አልፎ ስራው ተጠናቅቆ ወደ ህዝብ ጥቅም ማዋል የአንድ መንግሥት መለኪያ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የምንናገረው ወደ ተግባር መቀየር የኢትዮጵያ መንግሥት መታወቂ ነው ያሉ ሲሆን፤ እስካሁን በኢትዮጵያ ነበር አሁን በአፍሪካም የኢትዮጵያ መንግሥት የሚናገረውን ይፈጽማል የሚል እሳቤ እየጎላ መጥቷል ብለዋል፡፡
የትራንስፖርት ወጪ ከቀነስን፤ አሁን በተጀመረው የቤት ፕሮግራም በተቻለ መጠን ቤት ማቅረብ ከቻልን፤ ምግብ ላይ የጀመርነውን ስራ ከሰራን ለውጥ እናመጣለን ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ምግብ፣ ትራንፖርት እና ቤት ሰውን እያሰቃየ መሆኑን ጠቁመው፤ እነዚህ ሦስት ጉዳዮች እየተፈቱ ሲሄዱ ሰዎች ባላቸው ገቢ ልክ የተሻለ ኑሮ የሚያስችል እድል እንደሚያገኙ አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ተስፋ በብዙ መንገድ እየታየ መሆኑን ጠቅሰው፤ በልማቷ በጣም አመርቂ ውጤቶች እየታዩ ነው ብለዋል፡፡
መጪው ጊዜ ለልጆቻችን እና ለኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪና ብሩህ ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ከጥረት፣ ከስራ እና ከትጋት ውጪ የሚገኝ ውጤት እንደሌለ አንስተው፤ በልፋት ብቻ ነው ሀገር የምንቀይረው ብለዋል፡፡
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

