አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመዲናዋን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማዘመን ዘርፈ ብዙ ስራ እየተከናወነ ነው አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ዛሬ የመጀመሪያዎቹ 26 የከተማ አውቶብሶች ከነዳጅ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ ተለውጠው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ሥራ ጀምረዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የመዲናዋን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማዘመን ዘርፈ ብዙ ጥረት እያደረግን እንገኛለን፡፡
የከተማ አውቶቡስ የምናቀርበው በከፍተኛ ገንዘብ፣ በቢሊየኖች ድጎማ እና በማህበረሰቡ ወጪ ቢሆንም ተደራሽነታችንን በብዙ እጥፍ ማሳደግ እንዳለብን ተገንዝበን በትኩረት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ነባሮችን አውቶቡሶች ውስጣቸውን ወደ ተፈጥሮ ጋዝ በመቀየር እንዲሰሩ አድርገናል ነው ያሉት፡፡
ዛሬ ስራ እንዲጀምሩ የተደረጉት በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩት አውቶቡሶች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎችን ጫና እንደሚቀንስ አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም የዚህን ውጤታማነት መነሻ በማድረግ ስራው በቀጣይ የሚሰፋ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በትዕግስት ግዛቸው

