Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል የተቋማት ጥምረት ውጤት እያስገኘ ነው

ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል የተቋማት ጥምረት ውጤት እያስገኘ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ከ2017 ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው የሥነ ምግባር ግንባታና የሙስና መከላከል የተቋማት ጥምረት ውጤት እያመጣ ነው አሉ የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ አማረ ሰጤ።
በጥምረቱ መድረክ ላይ አፈ ጉባኤ አቶ አማረ ሰጤ እንዳሉት÷ ጥምረቱ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሥነ ምግባር ግንባታን ለማሳደግና በተቋማት ውስጥም ብልሹ አሠራርን ለመከላከል ትልቅ አቅም ነው።
ሙስናና ብልሹ አሠራርን መከላከል የአንድ ተቋም ሥራ ብቻ አለመሆኑን አንስተው ከግንዛቤ ፈጠራ ባሻገር ዘመናዊ አሠራርን በመተግበር መግታት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
ተቋማት አገልግሎታቸውን ዲጂታላይዝ እያደረጉ መሆናቸው እና በመሶብ አንድ ማዕከል ተደራሽ እየሆኑ መምጣታቸው ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል አስቻይ ሁኔታ እየተፈጠረ ነውም ብለዋል።
የክልሉ ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀብታሙ ሞገስ በበኩላቸው÷ ሙስናና ብልሹ አሠራርን መከላከል እንደ ሀገር ልዩ ትኩረት የተሰጠውና ከሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ዐበይት አጀንዳዎች መካከልም አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮሚሽነሩ ተቋማት የሠራተኞቻቸውን ሥነ ምግባር መገንባታቸው እና በሙስና የተገኘ ሀብት እንዲመለስ የማድረግ ተግባር ጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በክልሉ የሚገኙ 51 ተቋማት ለጋራ ዓላማ የተሰባሰቡበት ጥምረቱ በየተቋማቱ ሙስናና ብልሹ አሠራር ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው በማስቻሉ በ2018 በጀት ዓመት በሙስና መከላከል ተግባር ከ88 ሚሊየን ብር በላይ በኦዲትና በጥቆማ ማስመለስ እንዳስቻለም በመድረኩ ተገልጿል።
በደሳለኝ ቢራራ
Exit mobile version