አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የድንቅ ታሪክ፣ የጥንታዊ ስልጣኔ እና የነጻነት ምድር ናት።
የዚህች ታላቅ ሀገር ሉዓላዊነት እና ጸንቶ መኖር ምስጢር ደግሞ አንዱና ዋነኛው የሀገሪቱ መከላከያ ሠራዊት የጀግንነት ተጋድሎ ነው።
ሠራዊቱ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ የመጣውን የአሸናፊነት መንፈስ እና የጀግንነት ወርቃማ ታሪክ ይዞ፣ ዛሬ ላይ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል እና በሥነ-ልቦና ከፍታ ላይ ደርሷል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጥንካሬ ምስጢር የሚጀምረው ከህዝባዊነቱ ነው።
ሠራዊቱ የህዝብ ልጅ፣ የህዝብ አገልጋይ እና የህዝብ ጋሻ ነው። ከህዝቡ ጋር ያለው ጥልቅ ፍቅር እና ትስስር የማይናወጥ የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና ፈጥሮለታል።
በማንኛውም ፈታኝ ወቅት ሀገርን ከውጭም ሆነ ከውስጥ አደጋዎች ለመጠበቅ የተላበሰው ቁርጠኝነት የሚመነጨው ከዚህ ከኃያል የህዝብና የሀገር ፍቅር ስሜቱ ነው።
በፈተናዎች ውስጥ ሲያልፍ የሚጠነክረው፣ በድሎችም ጊዜ በርህራሄ፣ በትህትና እና በኃላፊነት ስሜት በአሸናፊነት ህዝቡን የሚያገለግለው በዚህ የሞራል ልዕልና ነው።
የዘመኑ ጦርነት የብዛት ብቻ ሳይሆን የጥራት፣ የስሜት ብቻ ሳይሆን የዕውቀት እና የቴክኖሎጂ አቅም ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ይህንን እውነት በመገንዘብ የሰው ኃይሉን በዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስ፣ ስትራቴጂ እና የትምህርት ዝግጅት አብቅቷል።
በወታደራዊ ማሰልጠኛዎች የሚሰለጠነው ሠራዊት ከዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሁም ከዘመኑ ጋር የተጣጣመ ዕውቀትና ክህሎት ያለው በመሆኑ፣ የሀገሪቱን ሰላም በብቃት ለመጠበቅ እና ማንኛውንም ተልዕኮ በስኬት ለመወጣት ስንቅ ሆኖታል።
የመከላከያ ሠራዊቱን አጠቃላይ አቅም ከፍ ካደረጉት ዋና ዋና ምሰሶዎች መካከል የአየር ኃይሉ የቴክኖሎጂ ዕድገት ይጠቀሳል። ሰማዩን በጽኑ ዘብነት የሚጠብቀው የአየር ኃይሉ ዛሬ ላይ የዓለምን ትኩረት የሳቡ እጅግ ዘመናዊ የጦር ጀቶችን መታጠቅ ችሏል።
ሱ-35 አራተኛ++ ትውልድ የጦር ጀቶች፡ የዘመናዊ አየር ትግል ኃያላን የሆኑት እነዚህ ጀቶች የሠራዊቱን የአየር ላይ የበላይነት እና ሉዓላዊነትን የማስከበር አቅም ወደ ሌላ ከፍታ አሸጋግረውታል።
በክትትል፣ በቅኝት እና በትክክለኛ ዒላማ መቺነት የሚታወቁ ዘመናዊ ድሮኖች የትጥቅ አካሉ በመሆናቸው የሠራዊቱን የመከላከል እና የማጥቃት አቅም ዘመናዊ አድርገውታል።
የሀገሪቱን ድንበር ደህንነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ እጅግ የላቁ የአየር መከላከያ ሲስተሞች በመዘርጋታቸው ደግሞ ሀገሪቱን አይነኬ አድርገዋታል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዛሬ የደረሰበት የብቃት ደረጃ ለአንዲት ሀገር ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ትልቅ ዋስትና ሆኗል።
በምሥራቅ አፍሪካም ሆነ በአህጉሪቱ ደረጃ በሰው ኃይል ብቃት፣ በዲሲፕሊን እና በዘመናዊ የጦር መሳሪያ ትጥቅ ቀዳሚ ሰራዊት መሆኑ ለአህጉሪቱም ደህንነት መጠበቅ አስተማማኝ ጋሻ ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የዛሬው ገጽታ የትናንት ጀግንነት ማስቀጠያ ብቻ ሳይሆን የነገዋን የበለጸገች እና የተከበረች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ጽኑ ዋስትና ነው።
ህዝባዊነቱን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ አቅሙ ጋር አስተሳስሮ የቀጣናው ደጀን መሆኑን ያስመሰከረው ሠራዊቱ የኢትዮጵያ ህዝብ የደህንነት አለኝታ እና የኩራት ምንጭ ነው።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በመልካም ፈቃዱ

