አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ወታደራዊ ሳይንስ እና ልምድ ለጦር ሜዳ ብቻ የተወሰኑ አይደሉም፤ ይልቁንም የመንግሥት ባለሥልጣናትን እና የሕዝብ አገልጋዮችን አቅም በማጎልበት ሀገራዊ ልማትንና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ዕሴቶች ናቸው።
እንደ ዌስት ፖይንት፣ ሮያል ሚሊተሪ ኮሌጅ እና የአሜሪካ ጦር ኮሌጅ የመሳሰሉ ታዋቂ ዓለም አቀፍ የወታደራዊ ትምህርት ተቋማት ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ ወታደራዊ ሳይንስና ሕይወት የሚሰጠው የዲሲፕሊን፣ የስነ-ምግባር እና የውሳኔ አሰጣጥ ልምድ ለሲቪል መሪዎችና ለፐብሊክ ሠራተኞች ትልቅ አቅም ይፈጥራል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት፤ የመደመር መንግሥት አመራሮች በሁርሶ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ሥልጠና በመውሰድ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የመደመር ሥልጣኔ ታላቁን ስትራቴጂ ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል፣ ከወታደራዊ ሳይንስና ሕይወት የምንቀስማቸው እውቀቶች፣ ክህሎቶች እና ልምዶች አሉን የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለይም ደግሞ በአንድ ሰዋሰው ለመግባባት፣ ሥነ ምኅዳርን በሚገባ ለመጠቀም፤ በተከታታይ ሕዝብን ለዓላማና ለተግባር ለማነጽ፤ ለሕዝብ የገባነውን ቃል በሚገባ አከናውኖ ለመጨረስ፤ ሁሉንም መዋቅር ለሀገራዊ ዓላማ ለማሰለፍ ይረዳል ብለዋል፡፡
ወታደራዊ ሥልጠናው ለማንኛውም አካል የማትበገር ጽኑ ሀገር መገንባት፤ ተተኪ ትውልድን ማፍራት እና የሀገርን ደኅንነት ምንጊዜም ማረጋገጥ የሚሉትን የስትራቴጂውን ሐሳብ በተገቢው መንገድ ለመረዳትም ሆነ ለማስፈጸም የማይናቅ ሚና እንደሚጫወት ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ለመገንባት እንችል ዘንድ ቁሳዊና መንፈሳዊ ብልጽግና፣ ባህላዊና ሞራላዊ ብልጽግና የተሸመኑበት ሁለንተናዊ ብልጽግና መገንባት አለብን ሲሉ አስገንዝበዋል።
ለዚህ ደግሞ አመራሩ ሁለንተናዊ ዝግጁነት ያስፈልገዋል፡፡ በአካል የዳበረ፣ በሞራል የጠነከረ፣ በዕውቀት የተሳለ፣ በጥበብ የበሰለ እንዲሆን ይጠበቅበታል፡፡ በተለይም በሀገር ፍቅር ስሜትና በሕዝብ ተቆርቋሪነት መንፈስ ግዴታዎቹን እንዲወጣ የሀገር አደራ ጥብቅ ነው ሲሉ በመልዕክታቸው አስፍረዋል፡፡
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

