አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) እኤአ በ2010 በሲንጋፖር መካሄድ ጅማሮውን ያደረገው የዓለም ወጣቶች ኦሊምፒክ ዛሬ ምሽት 3ከ30 በሴኔጋል ዳካር ይጀመራል።
በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው 4ተኛ የወጣቶች ኦሊምፒክ ኢትዮጰያ በአትሌቲክስ ፣በውሃ ዋና፣ በቴኳንዶ፣ በውሹና በብስክሌት ስፖርቶች ትካፈላለች፡፡
እ.ኤ.አ 2010 ለመጀመሪያ ጊዜ ሲንጋፖር በተካሄደው የወጣቶች ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስና በውሃ ዋና ስፖርቶች በ7 ልኡካንን የወከለች ሲሆን 2 ወርቅና 3 ነሀስ በድምሩ ሜዳልያዎችን አስመዝግባ ነበር።
እ.ኤ.አ 2014 ለሁለተኛ ጊዜ በቻይና ቤንጂንግ በተካሄደው እና ከ3580 በላይ ተሳታፊዎች በተካፈሉበት የወጣቶች ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ስፖርት ብቻ በ15 ተሳታፊዎች 3 ወርቅ 2 ብርና 3 ነሃስ በድምሩ 8 ሜዳልያዎችን አስመዝግባ ተመልሳለች ።
የአርጀንቲናዋ ቦነስ አይረስ እ.ኤ.አ 2018 3ኛውን የወጣቶች ኦሊምፒክ ያስተናገደች ሲሆን ኢትዮጵያ 2 ወርቅ፣ 2 ብርና 4 ነሀስ በድምሩ 8 ሜዳልያዎች አግኝታለች።
በኮሮና ቫይረስ መከሰት ምክንያት የተገፋው 4ኛው የወጣቶች ኦሊምፒክ በዛሬው እለት በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ ካለፋት ሦስት ውድድሮች ካስመዘገበችው ሜዳሊያዎች የተሻለውን ውጤት ለማስመዝገብ ዳካር ደርሳለች ።
ውድድሩ በዳካር፣ ዲያምኒያዲዮ እና ሳሊ በተሰኙ ሦስት የውድድር ማዕከላት በሚካሄደው ሲሆን ከ206 በላይ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች የተወከሉ 2,700 ያህል ወጣት አትሌቶች ይሳተፋሉ።
ውድድሩ ምእራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ዳካር ላይ ከጥቅምት 21 እስከ ህዳር 4 ድረስ ይከናወናል፡፡
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በነበሩ የወጣቶች ኦሊምፒክ ተሳትፎ 7 ወርቅ፣ 8 ብር እና 6 ነሐስ በድምሩ 21 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ከዓለም 31ኛ ከአፍሪካ ደግሞ ኬንያን ተከትላ 2ኛ ደረጃን ላይ ትገኛለች።
በወርቅነህ ጋሻሁን

