አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሁዋዌ የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይና ብሔራዊ የልማት ግቦቻችንን ለማሳካት በምናደርገው ጥረት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከተ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የሁዋዌ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን በቅርቡ ስራ ከጀመሩት ኤሪክ ዩዋን ጋር ተወያይተዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ጉዞ ከሁዋዌ ጋር በትብብር፣ በብሔራዊ ባለቤትነት፣ በዘላቂነት፣ በደህንነትና በአካባቢያዊ እሴት ፈጠራ መርሆዎች ላይ በመመስረት በሚሠሩ የትብብር መስኮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።
ሁዋዌ የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይና ብሔራዊ የልማት ግቦቻችንን ለማሳካት በምናደርገው ጥረት ውስጥ፣ በተለይም በአይሲቲ መሠረተ ልማትና በግንኙነት ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
የህዋዌ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኤሪክ ዩዋን መንግሥት የኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞ ለማስቀጠልና ለማፋጠን እየሠራቸው ያሉ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሥራዎች እጅግ አበረታች መሆናቸውን አንስተዋል።
የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታችን በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ሁዋዌም ለዚህ ዕድገት የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ እና ያለንን የሥራ ግንኙነት አጠናክረን ለመቀጠል ተስማምተናል ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

