Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል የዓለም አቀፍ የተጓዦች ትስስር ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሊደረግ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከልና ወንጀለኞች ተላልፈው እንዲሰጡ ለማድረግ ዓለም አቀፍ የተጓዦች ትስስር ቴክኖሎጂን ልትተገብር ነው አሉ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል።
ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እንዳሉት÷ ዓለም አቀፍ ወንጀሎች በቴክኖሎጂ የታገዙና ውስብስብ በሆኑበት ዘመን ዓለም አቀፋዊ ወንጀሎች ለመቆጣጠርና ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ አቅም መገንባት ያስፈልጋል።
በዚህም ኢንተርፖል ድንበር ዘለል ወንጀሎችን መከላከልና ወንጀል ሰርተው የተደበቁ አካላት ተላልፈው የሚሰጡበት ዓለም አቀፍ የተጓዦች ትስስር ቴክኖሎጂ ስርዓት ማልማቱን ገልጸዋል።
ቴክኖሎጂው በሽብርተኝነት ወይም በሌላ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል የሚፈለጉ አካላትን በየትኛውም ሀገር ላይ በቀላሉ ለመቆጣጠር እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀለኞችን ባሉበት ቦታ ለመያዝ ከኢሚግሬሽንና አየር መንገድ ጋር በሚኖረው ቅንጅት ላይ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋው ተግባባዊ ለማድረግ በሂደት ላይ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እንዲጠናከር በማድረጋቸው ከኢንተርፖል ጋር ጥብቅ ትብብር መፍጠር ማስቻሉንም ጄኔራሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከኢንተርፖል ጋር በሰራው የተቀናጀ ዘመቻ አንድ ወንጀለኛ ተይዞ ለኢትዮጵያ ተላልፎ እንዲሰጥና ለህግ እንዲቀርብ መደረጉን እና ኢትዮጵያም በተለያዩ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች የሚፈለጉ አካላትን ህግና ስርዓት በመከተል ለሀገራት ተላልፈው እንዲሰጡ ማድረጓን አስረድተዋል።
ቴክኖሎጂው በቀን በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችን በመከታተል ወንጀለኞችን በቀላሉ በቁጥጥር ስር ለማዋል ወሳኝ መሆኑን እና በትራንስፖርት ዘርፎች የሚስተዋሉ የሽብር እንቅስቃሴዎችና ወንጀሎችን ተከታትሎ መያዝ እንደሚያስችል ገልጸው በቅርቡም ተግባራዊ እንደሚደረግ መጠቆማቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
በኢንተርፖል የለማው ይሄው ዓለም አቀፍ የተጓዦች ትስስር ቴክኖሎጂ ሥርዓት ሽብርተኝነትና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ሰርተው የተደበቁ ወንጀለኞች ሕግን ተከትሎ ለአባል ሀገራት ተላልፈው እንዲሰጡ ማድረግ የሚያስችል ነው።
Exit mobile version