Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የአዕዋፍ ቱሪዝም አቅም አላት ─ የቱሪዝም ባለሙያዎች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ካሉ ከፍተኛ የአዕዋፍ ቱሪዝም አቅም ካላቸው ሀገራት አንዷ ናት አሉ በአእዋፍ ጥናትና ቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች፡፡
የአዕዋፍ ሳይንቲስትና የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ባለሙያው ይልማ ደለለኝ÷ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ከፍተኛ የአዕዋፍ ዝርያ ካላቸው ሀገራት በ4ተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ይናገራሉ፡፡ በአጠቃላይ በሀገራችን ከ872 በላይ የአእዋፍ ዝርያዎች እንዳሉና ከነዚህ ውስጥ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ 20 ብርቅዬ ዝርያዎች መገኛ ናት ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ከፍተኛ የአዕዋፍ ዝርያዎች ቁጥር ቢኖራትም፣ ወደ ሀገሪቱ የሚገቡት የአእዋፍ ጎብኝዎች ቁጥር ከኬንያ፣ ታንዛኒያ ወይም ደቡብ አፍሪካ ጋር ሲነጻጸር እጅግ አናሳ መሆኑን አቶ ይልማ ያነሳሉ፡፡
የቱሪዝምና የአዕዋፍ ጉብኝት መሪው ኢያሱ ተስፉ በበኩላቸው እንደ የባሌ ተራሮች፣ ያቤሎ፣ አዋሽ፣ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆችና ጋምቤላ ረግረጋማ ቦታዎች የመሳሰሉ ከፍተኛ የወፍ ጉብኝት ፍላጎቶችን ለማርካት የሚያስችሉ መዳረሻዎች ቢኖሩም ከሀብቱ በሚገባ እየተጠቀመች ነው ለማለት አያስደፍርም ብለዋል።
ሌላኛው የወፍ ጉብኝት ባለሙያው አቶ አቤል በላይ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ከአዕዋፍ ሀብቷ ተጠቅማለች ወይ ለሚለው ጥያቄ ፈጽሞ አልጀመረችም ብንል ይሻላል ሲሉ ያሰምሩበታል፡፡ አቶ አቤል አክለውም ከዘርፉ የሚገኘው ውጤት በሚገባ በመንግሥት ታቅዶ ተሰርቶበት ሳይሆን በተወሰኑ ግለሰቦች ጥረት የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከፍተኛ የአዕዋፍ ዝርያ ስብጥር፣ የተለያዩ የተፈጥሮ መልክዓ ምድሮችና ሥነ-ምህዳሮች ተደምረው ኢትዮጵያን ለአዕዋፍ ቱሪዝም ምቹ መዳረሻ እንድትሆን አስተዋጽኦ አድርገዋል ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ የዱር ሕይወት ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ ናቃቸው ብርሌው ናቸው።
የኢትዮጵያ የዱር ሕይወት ባለሥልጣን ሀገሪቱ ከዘርፉ በአግባቡ ተጠቃሚ ለማድረግ የአዕዋፍ ቱሪዝም መዳረሻዎችን የመለየትና ማስተዋወቅ፣ የተሟላና ተደራሽ የአዕዋፍ ቱሪዝም መረጃ ማዘጋጀት እንዲሁም የሰው ኃይልና የባለሙያዎችን አቅም የማጠናከር ሥራዎች እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከምርምር ተቋማት፣ ከአጋር ድርጅቶችና ከአጠቃላይ የግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር የአዕዋፍ ምልከታ፣ የዝርያ መለያ፣ የጎብኚዎች አቀባበል እና የቱሪዝም አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተመሠረተ የሥልጠናና የአቅም ግንባታ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አንስተዋል፡፡
በተለይም በጥብቅ ቦታዎች አካባቢ የሚኖሩ ማኅበረሰቦችን በአካባቢ አስጎብኚነት፣ በእንግዳ ማስተናገድና በሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶች በማሳተፍ ከዘርፉ ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ሥራዎች እየሠሩ ናቸው ብለዋል።
አቶ እያሱ ተስፉ ከዘርፉ በተገቢው ለመጠቀም “የአእዋፍ ቱሪዝምን ለማሳደግ የብሔራዊ የወፍ መረጃ ሥርዓት መገንባት፣ ለዓለም ገበያ የተዘጋጁ የጉዞ መርሃ-ግብሮችን ማቅረብ፣ የአካባቢ ማኅበረሰቦችን ማሳተፍና የተፈጥሮ ጥበቃን ከቱሪዝም ገቢ ጋር ማገናኘት ያስፈልጋል” ሲሉ ይመክራሉ፡፡
“የአእዋፍ መዳረሻ አካባቢዎችን፣ ደኖችን፣ ረግረጋማ ቦታዎችን ከሰው ሠራሽ ጉዳትና ከወረራ መጠበቅ እንዲሁም የጥበቃ ሥራዎችን ለአካባቢው ሕብረተሰብ በማስተማርና በማሳተፍ የላቀ ውጤት ማምጣት ይቻላል” የሚሉት ደግሞ አቶ ይልማ ናቸው፡፡
የወፍ አስጎብኚው አቤል እንዳሉት፣ ሥነ-ምህዳሩን የማስተጠበቅ አቅማችን እየጨመረ በመጣ ቁጥር እና ግንዛቤ ያለው ማኅበረሰብ እየፈጠርን በመጣን ቁጥር፣ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአዕዋፍ ቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ ተጠቃሚ መሆን ትችላለች ብለዋል፡፡
የአዕዋፍ ቱሪዝም ማለት አዕዋፋትን መመልከት ብቻ ሳይሆን፣ የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ ለሀገር ኢኮኖሚና ለማኅበረሰቡ ዘላቂ ጥቅም የሚፈጥር የልማት አማራጭ መሆኑን አቶ ናቃቸው አስገንዝበዋል፡፡
የአዕዋፍ ሀብት የተፈጥሮ ውበት ብቻ ሳይሆን፣ በትክክል ከተጠበቀና ከተደራጀ ለሥራ ፈጠራ፣ ለውጭ ምንዛሬ ገቢ፣ ለማኅበረሰብ ተጠቃሚነትና ለሀገር ዘላቂ ቱሪዝም የሚያገለግል ሀብት ነው። ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ እየተገበረችው ያለው ሥነ-ምህዳር ልማትና እንክብካቤ ለአዕዋፍ ሀብት ማደግና ከዘርፉ የሚገኘውን ጠቀሜታ ለማሳደግ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።
በቴዎድሮስ ሳህለ
Exit mobile version