Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጂኦፖለቲካዊ ተጽዕኖው ከፍ እያለ የመጣው የኢትዮጵያ ባህር ኃይል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ባህር ኃይል በፈረንጆቹ 2018 ከተቋቋመ በኋላ አሁን ወቅት ተቋማዊ አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ እያሳደገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ባህር ኃይል በታሪክ በምሥራቅ አፍሪካ እና በቀይ ባህር ቀጣና ላይ ከፍተኛ ዝና፣ ግርማ ሞገስ እና ጠንካራ ወታደራዊ አቅም የነበረው የጦር ኃይል ክፍል ነበር።

በ948 ዓ.ም የተገነባው የኢትዮጵያ ሮያል ባህር ኃይል ወይም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባህር ኃይል ዋና ቋሚ የጦር ሰፈር እና ማሰልጠኛው በምፅዋ ወደብ ላይ የነበረ ሲሆን በአሰብ እና በዳህላክ ደሴቶች ላይ ትልልቅ የባህር ኃይል የጦር ሰፈሮች ነበሩት።

ይሁን እንጂ በፈረንጆቹ 1993 ኤርትራ መገንጠሏን ተከትሎ የባህር ኃይሉ ለሦስት አስርት ዓመታት የፈረሰ ሲሆን የኢትዮጵያ ባህር ኃይል መርከቦች ወደ ተለያዩ የጎረቤት ሀገራት ወደቦች መሰደዳቸውን ታሪክ ያስረዳል።

ለተወሰኑ ዓመታት የኢትዮጵያ መርከቦች በየመን ወደቦች ተጠልለው የቆዩ ቢሆንም በ1993 የመን እንዲወጡ ስታደርግ የመርከቦቹ መዳረሻ ጅቡቲ እንደሆነች ፍራንዝ አማደስ ዶምብሮስኪ “Ethiopia’s Access to the Sea” በሚለው መፅሁፉ ላይ አስረድቷል።

መርከቦቹን በዓሰብ ወደብ ለማቆየት ከኤርትራ ጋር የተደረገው ድርድር ባለመሳካቱ አብዛኞቹ መርከቦች በጅቡቲ ወደብ የቆሙበትን ዕዳ ለመክፈል በጨረታ ተሸጠዋል፤ አንዳንዶቹም እንዲፈራርሱ መደረጋቸውን ገልጿል።

በመጨረሻም ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ባህር አልባ ሀገር መሆኗን ተከትሎ የቀድሞው የኢትዮጵያ ባህር ኃይል በይፋ እንዲፈርስ ተደርጓል።

 

ይሁን እንጂ የመደመር መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ የባህር ኃይል እንደገና የተቋቋመ ሲሆን በሀገሪቱ ስትራቴጂካዊ ፍላጎት፣ በጂኦፖለቲካዊ ተጽዕኖ እና በቀጣናዊ የደህንነት ትብብር ላይ ትልቅ ለውጥ እያመጣ ይገኛል።

 

ባህር ኃይሉ በቢሾፍቱ ራሱን የቻለ ዘመናዊ የባህር ኃይል አካዳሚ እና ማሰልጠኛ ማዕከል እንዲሁም እጅግ ዘመናዊ ዋና መሥሪያ ቤት ገንብቶ ያጠናቀቀ ሲሆን ተቋሙ በቴክኖሎጂና በሥነ ልቦና የታነጹ ብቁ ባህርተኞችን በማፍራት ላይ ይገኛል።

በዲፕሎማሲ እና ቀጣናዊ ትብብር ረገድ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል የየመን፣ ኦማን፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊላንድ እና ፑንትላንድ የባህር ኃይል አዛዦች የተሳተፉበትን የአራት ቀናት ቀጠናዊ የባህር ላይ ፎረም በአዲስ አበባ አስተናግዷል።

በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ዋና አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ÷ ኢትዮጵያ ወደ ባህር በር የመመለስ ጉዞ የማይቀር መሆኑን ጠቅሰው በመሆኑም ተቋሙን ማጠናከር የሀገሪቱን የንግድ መርከቦች፣ የኢኮኖሚ ጥቅሞች እና የቀይ ባህርን ሰላም ለመጠበቅ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

በተጨማሪም የባህር ኃይሉን አቅም ለማሳደግ እንደ ሩሲያ እና ፈረንሳይ ካሉ አገራት ጋር የቴክኒክና የስልጠና ስምምነቶች የተደረጉ ሲሆን በአውሮፓ ህብረት አዘጋጅነት በተካሄደው የቀጠናው አዛዦች ፎረምም ተሳትፎ አድርጓል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የባህር ዳርቻ ባይኖራትም፣ የባህር ኃይሏ መዋቅር ግን ለወደፊቱ ስትራቴጂካዊ የባህር በር ይዞታ እና ለቀጣናው የጋራ ደህንነት አስተዋጽኦ ለማድረግ በከፍተኛ የሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ አቅም እየተገነባ ይገኛል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በሚኪያስ አየለ

Exit mobile version