Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ እውቅና

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በደማቅ ታሪክ የተቀረጸች፣ በተፈጥሮ የተዋበች፣ በልማት የምትታደስና ወደ ነገ በተስፋ የምትራመድ ከተማ ነች።
አንዳንድ ከተሞች በታሪካቸው ይነገራሉ፤ ሌሎች በተፈጥሮ ውበታቸው ይደነቃሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በሥልጣኔያቸውና በዓለም አቀፍ ተፅዕኗቸው ይታወቃሉ።
አዲስ አበባ ግን እነዚህን ሁሉ በአንድ ላይ ያቀፈች፣ ታሪክን ከዘመናዊነት፣ ተፈጥሮን ከከተሜነት፣ ጥንታዊ ግርማ ሞገስን ከነገው ተስፋ ጋር አጣጥማ የያዘች ልዩ ከተማ ናት፡፡
የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ መዲና፣ የዲፕሎማሲ ማዕከልና የአህጉሪቱ የአንድነት ምልክት ነች።
የአህጉሪቱ የጋራ ተስፋ የሚንጸባረቅባት የዲፕሎማሲ መድረክ የአፍሪካ ሕብረት ዋና መሥሪያ ቤትን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት መገኛ መሆኗ የከተማዋን ዓለም አቀፍ ዝናና ተቀባይነት ያጎላል።
ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ባለሀብቶችና ጎብኚዎች በከተማዋ የሚያገኙት ተሞክሮ አዲስ አበባን የአፍሪካ ዓለም አቀፍ መስኮት አድርጓታል።
አዲስ አበባ በ2026 የሻንሃይ ዓለም አቀፍ የዘላቂ ከተማ ልማት ሽልማት (Shanghai Award) አሸናፊ ከሆኑ አምስት ከተሞች አንዷ ሆናለች፡፡
በመደመር መንግሥት የተከወኑና እየተስፋፉ የሚገኙ የከተማ ልማት ስራዎች የአዲስ አበባን ገጽታ ይበልጥ በማሳመርና የነዋሪዎቿን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል።
የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከተማዋ የነበራትን ገጽታ ከማሳመር ባለፈ የከተማ ኑሮን የሚያዘምኑ አዳዲስ አማራጮችን ፈጥረዋል። በተለይ የእግረኛ መንገዶች መስፋፋት፣ የመንገድ ዳርቻዎች መዋብ፣ የአረንጓዴ ስፍራዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያና የሕዝብ መናፈሻ ስፍራዎች ግንባታ ከተማዋን ለነዋሪዎችና ለጎብኚዎች ምቹ እያደረጉ ይገኛሉ።
የኮሪደር ልማት ትልቁ ፋይዳ የከተማን ውበት በዓይን ከሚታይ ገጽታ በላይ ወደ ተግባራዊ የኑሮ ጥራት መቀየሩ ነው።
የዘመናዊ ከተማ ሥልጣኔ የሚለካው በህንፃዎች ብዛትና በመንገዶች ስፋት ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮን ከከተማ ኑሮ ጋር በማጣመር በሚፈጥረው ምቹ አካባቢ ጭምር መሆኑም ይታመናል።
በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻ ልማትና የአረንጓዴ መሠረተ ልማት ሥራዎች ለከተማዋ ውበትና ለነዋሪዎቿ የኑሮ ጥራት የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
የወንዝ ዳርቻዎችን በማልማት፣ አካባቢዎችን በማስዋብ፣ የአረንጓዴ ስፍራዎችን በማስፋፋትና የሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎችን በመፍጠር ከተማዋን የተፈጥሮ ውበት የተጎናጸፈች ዘመናዊ መዲና ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ቀጥሏል፡፡
አረንጓዴ ስፍራዎች ከአየር ንጽህና ባለፈ ለከተማ ውበት፣ ለአካባቢ ሚዛንና ለሰው ልጅ የአእምሮ ዕረፍት የሚኖራቸው ሚና የጎላ ነው።
ዜጎች ተመጣጣኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ለኑሮ ምቹ የሆነ መኖሪያ እንዲያገኙ ማስቻል የከተማ ልማት መሠረታዊ ግብ ነው።
ለኑሮ አመቺ ባልነበሩ የመኖሪያ ስፍራዎች ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ዜጎች በሰው ተኮር የልማት ስራዎች ወደ ዘመናዊና ምቹ የመኖሪያ ቤት ባለቤትነት ተሸጋግረዋል፡፡
በተለይ የተቀናጀ የቤት ልማት ከመኖሪያ ቤት ጋር የመንገድ፣ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የጤና፣ የትምህርትና የመዝናኛ አገልግሎቶችን በማጣመር የኑሮ ጥራትን ያሻሽላል። ይህ ደግሞ የከተማዋ ልማት ለሰው ልጅ የተቃኘ እንዲሆን አድርጓል።
ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው ወደ ሥራ፣ ወደ ትምህርት ተቋማት፣ ወደ ጤና ተቋማትና ወደ መዝናኛ ስፍራዎች በቀላሉና በደህንነት መጓዝ መቻላቸው የከተማ ሥልጣኔ አንዱ መለኪያ ነው።
ተደራሽ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ቀልጣፋ የትራንስፖርት ሥርዓት የዜጎችን ጊዜ ይቆጥባል፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ያበረታታል፣ የከተማዋንም የኑሮ ጫና ይቀንሳል።
በተለይም የእግረኛ መንገዶች፣ የብስክሌት መንገዶች፣ የሕዝብ ትራንስፖርትና ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ የሆኑ መሠረተ ልማቶች በተቀናጀ መልኩ መገንባታቸው ከተማዋን ለሁሉም የተመቸች ያደርጋታል።
አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ኩራት፣ የአፍሪካ የአንድነት ምልክትና የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማዕከል ከመሆኗ ባለፈ ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለጎብኚዎቿ ማራኪና ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለ ነገ የምታዘጋጅ ከተማ የመሆን ጉዞዋን በመቀጠል ላይ ትገኛለች።
አዲስ አበባ የዛሬን ልማት በቁርጠኝነት የምታስፋፋና የነገውን ብሩህ ተስፋ እየገነባች የምትገኝ የአፍሪካ ውብ መዲና ሆና ቀጥላለች፡፡
በመልካም ፈቃዱ
Exit mobile version