Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በክልሉ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው – አቶ ኃይሉ አዱኛ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው አሉ የክልሉ ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ።

አቶ ኃይሉ አዱኛ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ ፥ የኦሮሞ ሕዝብ ውስጣዊ አንድነቱንና ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር ያለውን ወንድማማችነት በማጠናከር የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች ሴራ ማምከን አለበት ብለዋል።

ክልሉ ያስመዘገባቸውን ድሎች ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የክልሉን ብሎም የሃገሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥ ለአምስት ዓመታት የሚቆይ ራስን የመቻል ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባራዊ አፈጻጸም መገባቱንም ጠቁመዋል።

ኃላፊው ዕቅዱ ክህሎትን ማሳደግና ሥራ ፈጣሪነትን ማበረታታት፣ ማሽነሪና ቴክኖሎጂን ማስፋፋት፣ የፋይናንስና የቁጠባ አቅምን ማጠናከር፣ በሁሉም ዘርፎች የኢንዱስትሪ ሽግግርን እውን በማድረግ ምርታማነትን ማሳደግ፣ እና የኦሮሞ ባህል ሕዳሴና ከተሜነትን እውን ማድረግ ላይ ያተኮረ መሆኑን አስረድተዋል።

ከጸጥታ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምስራቅ ዞን የሽርካ ወረዳ የጽምዶ ኃይሎች በፈጸሙት የሽብር ድርጊት የተጎዱ የሕብረተሰብ ክፍሎችን መልሶ ለማቋቋም እና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አቶ ኃይሉ ተናግረዋል።

የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ አዲስ ምዕራፍ መግታት የተሳናቸው ኃይሎች ተደራጅተው በሽብር ተግባር ላይ መሰማራታቸውን የጠቀሱት ኃላፊው ሸኔ ከጽምዶ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት የሽብር ተግባራትን ሲፈጽም የቆየና አሁንም እየፈጸመ ያለ ቢሆንም፣ መንግሥት እነዚህን እንቅስቃሴዎች በመከታተል በተለያዩ አካባቢዎች እያከሸፈና በሽብር ቡድኖቹ ላይ ጠንካራ ርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ይሁን እንጂ ጥቅምት 14 ቀን 2019 ዓ.ም. በሽርካ ወረዳ በብርቦ ጮሌ ቀበሌ እነዚህ ኃይሎች ራሳቸውን መከላከል በማይችሉ ንጹሐን ዜጎች ላይ ጥቃት በማድረስ ወደር የሌለው የጭካኔ ተግባር መፈጸማቸውን የገለጹት አቶ ኃይሉ በዚህ አሳዛኝ ድርጊት የንጹሐን ዜጎች ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ማለፉን፣ የሕዝብና የመንግሥት ንብረት መቃጠሉን፣ እንዲሁም ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸውና ከንብረታቸው መፈናቀላቸውን አብራርተዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በተከናወነው የኦፕሬሽን ሥራ 73 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝና የጽምዶ ኃይል እንቅስቃሴ ሲያደርግባቸው የነበሩ ስድስት ቀበሌዎችን ማጽዳት መቻሉን አንስተዋል።

አቶ ኃይሉ መንግሥት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም በተለይም አፋጣኝ ድጋፍና ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ተለይተው እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሆነ፣ የምግብ አቅርቦት በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝና ዜጎችን ወደ ቀደመ ቀያቸው ለመመለስ በትኩረት እየተሠራ እንደሆነ አመልክተዋል።

አክለውም ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተደረጉ ውይይቶች ሕዝቡ የጽምዶ ኃይሎችን ድርጊት በጽኑ ማውገዙንና የክልሉ መንግሥትም ከዜጎች መፈናቀልና መልሶ ማቋቋም ጎን ለጎን በእነዚህ ኃይሎች ላይ እየወሰደ ያለውን የሕግ ማስከበር ርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በሲፈን መኮንን

Exit mobile version