አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በረጅም ጊዜ የልማት እቅዷ ውስጥ ለሰው ሀብት ልማትና ለሴቶች እኩልነት መረጋገጥ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው አሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አህመድ ሽዴ፡፡
በህዝብ ቁጥርና ልማት፣በስነ-ተዋልዶ ጤናና መብቶች እንዲሁም በጾታ እኩልነት ፖሊሲ ላይ ያተኮረው የአፍሪካ-እስያ ፓርላማ አባላት የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ አፈ-ጉባኤው ኢትዮጵያ እስከ እ.ኤ.አ 2050 በሚዘልቀው «የመደመር» ስትራቴጂ አማካይነት ሙሉ ሀገራዊ አቅሟን፣ህዝቧን፣ ተቋሞቿንና ሀብቷን በማቀናጀት ለጋራ ሀገራዊ ግብ በቁርጠኝነት እየሰራች እንደምትገኝ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ሀገር በቀል በሆኑ እሳቤዎች ላይ የተመሰረቱ የልማት መፍትሄዎችን እንዲሁም በሃሳብ፣በስትራቴጂና በተጠያቂነት የሚመራ ዘመናዊ አስተዳደርን በውጤታማነት እየተገበረች ነው ብለዋል።
የመደመር መንግሥት ይህንን ግዙፍ የረጅም ጊዜ ርዕይ ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመለወጥ አዳዲስ መፍትሄዎችን በመፍጠር፣ የአገልግሎትና የልማት አቅርቦትን በማፋጠን፣ ስኬታማ ስራዎችን በማስፋፋትና በመድገም እንዲሁም በሁሉም የልማት መስኮች ጥራትን በማረጋገጥ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
እነዚህ መርሆች በትምህርት፣ በጤና፣ በመሰረተ ልማት ግንባታዎችና በሌሎችም የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በተመሳሳይ ሁኔታ ስራ ላይ እየተተገበሩ እንደሆነም አመልክተዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ «ራስን መቻል» በሚል መርህ ውጫዊ ጫናዎችን መቋቋም የሚችሉ ጠንካራ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ተቋማዊ አቅሞችን በመገንባት፣የሚገጥሙ ፈተናዎችን ለሀገር እድገት ወደሚጠቅሙ ስትራቴጂካዊ እድሎች እየቀየረች ትገኛለች ብለዋል፡፡
የማንኛውም ሀገር ትክክለኛው የዕድገትና የጥንካሬ መሠረት በግንባታዎችና በተቋማት ብቻ አይወሰንም ያሉት አፈ ጉባኤው ዋናው አቅም የህዝቡ ጤና፣ትምህርት፣ክህሎትና ሰብዓዊ ክብር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዚህም ምክንያት የህዝብ ቁጥርና ልማት፣ የስነ-ተዋልዶ ጤናና መብቶች እንዲሁም የጾታ እኩልነት ጉዳዮች ሁለተኛ ደረጃ ጉዳዮች ሳይሆኑ፣ ሀገራዊ አቅምና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂው ማዕከል መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

