Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አካታች የከተማ ልማት ለዘላቂ ብልጽግና

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የከተማ ልማት ዋና ዓላማ ገጽታን ማሳመር ብቻ ሳይሆን ለነዋሪዎች የተሻለ የኑሮ ሁኔታ መፍጠር ነው።
በዚህ መሠረት አዲስ አበባ የቤት አቅርቦትን በማሳደግ፣ የልማት አሠራሯን በማሻሻልና የተለያዩ የመኖሪያ አማራጮችን በማቅረብ የነዋሪዎቿን ተጠቃሚነት እያሳደገች ትገኛለች፡:
አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከል በመሆኗ ያረጁ አካባቢዎችን በማልማት የሰው ልጅ የአኗኗር ክብርን የጠበቀና ከዓለም ጋር የሚወዳደር የኑሮ ዘይቤ የመፍጠር ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
የቤት ፍላጎትን ለማሟላት የሥራ ፍጥነትን ማሳደግ፣ የአሠራር ሥርዓቶችን ማዘመንና የመንግሥትና የግል ዘርፍን ትብብር ማጠናከር ወሳኝ ነው።
በዚህም የግል ባለሀብቶች፣ የሪል ስቴት አልሚዎችና ሌሎች አጋሮች በቤት ልማት ውስጥ የሚኖራቸውን ተሳትፎ በማሳደግ አቅርቦቱን ለማስፋት የሚያግዝ አቅጣጫ ተይዟል።
ዘመናዊ ቤቶች የነዋሪዎችን ፍላጎት በሚያሟላ ሁኔታ ማቅረብ፣ የኑሮ ምቾትን ማሳደግና የማህበራዊ አብሮነትን ማጠናከር መለኪያቸው እንደመሆኑ የጋራ መገልገያዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ የሕፃናት መጫወቻ ሥፍራዎች፣ ንጹሕ አካባቢ ያላቸው የመኖሪያ ሥፍራዎች የተሻለ የኑሮ ጥራት እንዲኖር ያግዛሉ።
ለአብነት በትናንትናው ተመርቆ ለነዋሪዎች የተላለፈው የቦሌ ሹቡ ኤጄርሳ የተቀናጀ የነዋሪዎች መንደር ከመኖርያ ህንፃዎች በተጨማሪ የወተት ላሞችን የሚይዙ ሼዶች፣ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ፣ የንግድ ሱቆች፣ ዘመናዊ የምርት ማከፋፈያና መሸጫ መጋዘን፣ ወፍጮዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳ፣ የሕፃናት መጫወቻና ማቆያ ማዕከል፣ የስብሰባ አዳራሽ እንዲሁም ሌሎችም መሠረተ ልማቶች ተሟልተውለታል።
ይህ ለልማት ተነሺዎች የተላለፈው የተቀናጀ የነዋሪዎች መንደር የነዋሪዎችን የገቢ ምንጭ የሚያሳድጉና በዘመናዊ መሠረተ ልማት ለማስቀጠል የሚያስችሉ አዳዲስ አውታሮችን የያዘም ነው፡፡
ከዚህ አንጻር በከተማዋ እየተገነቡ ለህዝብ በመተላለፍ ላይ የሚገኙ መኖሪያዎች የዘመናዊ አኗኗር መስፈርቶችን ያሟሉ ናቸው፡፡
በተመሳሳይ የቤት አቅርቦት ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ እንዲሆን ለልማት ተነሺዎች፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ለሀገር ባለውለተኞች ቅድሚያ መስጠትን ከተማ አስተዳድሩ ትኩረት ሰጥቶታል፡፡
ይህ ሰው ተኮር የልማት አቅጣጫ የከተማዋን ውበትና የልማት ፍጥነት ከዜጎች ተጠቃሚነት ጋር በማጣመር የተሻለ መኖሪያ፣ ንጹሕ አካባቢ፣ አካታችነት እና የዘላቂ ከተማ ብልጽግና ዋና መሠረቶች አድርጓል።
በምሕረት ደምሴ
Exit mobile version