Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በትግራይ ክልል የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ከጥቅምት 30 ጀምሮ ሊከፈል ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ)በትግራይ ክልል የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ከጥቅምት 30 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ ይከፈላል አለ የክልሉ ባለአደራ አስተዳደር፡፡
የክልሉ ባለአደራ አስተዳደር የኢኮኖሚና መልሶ ግንባታ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቴዎድሮስ አረጋይ (ዶ/ር) ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ የደመወዝ ክፍያውን ለማስፈጸም የፋይናንስ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
በሥራ ቦታቸው ተገኝተው ሥራ መጀመራቸውን ሪፖርት ላደረጉና በሕጋዊ ሁኔታ በመንግሥት ተቋማት ተቀጥረው ለሚሠሩ ሠራተኞች ደመወዝ እንደሚከፈል አስረድተዋል።
የደመወዝ ክፍያው መጀመር በክልሉ የመንግሥት ተቋማት ሥራ መልሶ ለማስጀመርና የሠራተኞችን የሥራ ተነሳሽነት ለማጠናከር ከሚደረጉ ጥረቶች አንዱ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ተቋማትን መልሶ የማቋቋምና አገልግሎት የማሻሻል ሂደት እንዲሁም በመቐለ ከተማ የመሶብ አንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት ለማስጀመር የሚደረጉ ዝግጅቶችም መጠናከራቸውን አመልክተዋል፡፡
በትግራይ ክልል ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች የደረሰውን ውድመት ተከትሎ የተቋረጡ አገልግሎቶችን መልሶ ለማስጀመር በሚደረገው ጥረት የተቋማት ሠራተኞች ወደ ሥራ ቦታቸው ተመልሰው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሥራቸውን እንዲጀምሩ፣ የመንግሥት ቢሮዎች ሥራ እንዲያከናውኑና የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲመለሱ የተለያዩ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የውሃ፣ የባንክና የኢንተርኔት አገልግሎቶችን መልሶ ለማስጀመርም ጥረቶች መደረጋቸው አንስተው፤ አሁን ላይ በከተማው ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ከተሠሩት ሥራዎች በመነሳት የተሻለ የአገልግሎት ፍጥነትና ጥራት ለማረጋገጥ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
በግዛቸው ግርማዬ
Exit mobile version