አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና ደኅንነት መልህቅ እንደመሆኗ በቀይ ባህር አካባቢ ህልውና እንዲኖራት መፈለጓ ተገቢ ነው አሉ በአፍሪካ የደኅንነት ጥናት ኢንስቲትዩት የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ዳይሬክተር ፖል ሲሞን ሃንዲ (ዶ/ር)፡፡
ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የጣና ፎረምን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በማስተናገድ የቀጣናው መልህቅ መሆኗን በተግባር አሳይታለች፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና ደህንነት ላይ ገንቢ ሚናን እየተወጣች መሆኑን ገልጸው፤የባህር በር ፍላጎቷ ቋሚ ፍላጎት እንደመሆኑ መጠን የመንግሥትን ሰላማዊ መንገድ የመከተል አካሄድ የሚደገፍ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር አካባቢ ውክልና እንዲኖራት መፈለጓ ተገቢ በመሆኑ ይህንኑ ፍላጎት ከቀንዱ ሀገራት ጋር በውይይትና በንግግር መፍትሄ መስጠት ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በናይጄሪያ የኦባፌሚ አዎሎዎ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ቻርለስ ዑኬጄ (ፕ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ኃይል መሆኗን ገልጸው፤ የባሕር በር ፍላጎቷ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሁሉን አሸናፊ በሚያደርግ መልኩ በውይይት ሊፈታ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት አስርት አመታት በቀጣናው ሰላምና ደህንነት ብቻ ሳይሆን በአስተዳደርና ቢዝነስ ዘርፍም ገንቢ ሽግግር ማድረጓን ጠቁመዋል፡፡

