Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከተሞቻችን ለቀጣዩ ትውልድም ዘላቂ የብልጽግና ውርስ እንዲሆኑ በጋራ እንሠራለን – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ)ከተሞቻችን ለቀጣዩ ትውልድም ዘላቂ የብልጽግና ውርስ እንዲሆኑ በጋራ እንሠራለን አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
በቅርቡ በቻይና ሻንሃይ ከተማ በተካሄደው የ2026 የሻንሃይ ዓለም አቀፍ የዘላቂ ከተማ ልማት ሽልማት ውድድር አዲስ አበባን ጨምሮ አምስት ከተሞች ተሸላሚ ሆነዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ የዘላቂ ከተማ ልማት መድረኮች ተከታታይ እውቅና እያገኘች ያለች ከተማ ናት ብለዋል፡፡
ከተማን መለወጥ የሚቻለው በግልጽ ርዕይ፣ በተቀናጀ ጥረትና የሰው ልጅን ሕይወት ማዕከል ባደረገ የልማት አቅጣጫ መሆኑን ጠቅሰው፤ አዲስ አበባም ይህንን እሳቤ በተግባር እየተረጎመች መሆኗን በዓለም አቀፍ መድረክ ዳግም አስመስክራለች ነው ያሉት።
ይህ ሽልማት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአራተኛ ጊዜ የተዘጋጀ ሲሆን፤ አዲስ አበባ በአራቱ ዙሮች ሁለት ጊዜ እውቅና አግኝታለች። በ2024 የሴኡል ስማርት ሲቲ ሽልማትን፣ በ2026 ደግሞ የሻንሃይ ዓለም አቀፍ የዘላቂ ከተማ ልማት ሽልማትን ማግኘቷን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በ2023 አዲስ አበባ በምገባ ፕሮግራምና በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ዘርፎች ፈጣን ለውጥ እያስመዘገበች ያለች ከተማ በመሆኗ ዓለም አቀፍ እውቅናና ሽልማት ማግኘቷን አመልክተዋል።
ይህ እውቅና ለሀገራችን ታላቅ ክብር ከመሆኑም በላይ እየሠራን ላለነው ሥራ ብርታትና ተጨማሪ ተነሳሽነት የሚሰጥ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ከሁሉም በላይ በከተማችን የምንተገብራቸው ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች፣ የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃና የአኗኗር ሁኔታ ለማሻሻል የምናደርገው ጥረት፣ እንዲሁም የከተማዋን የተፈጥሮና ማኅበራዊ ፀጋዎች ወደ ልማትና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የመቀየር ሥራችን ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የሚያረጋግጥ ዓለም አቀፍ ምስክርነት ነው ብለዋል።
የመደመር እሳቤያችንም ልማትን ከሰው ሕይወትና ደኅንነት ጋር አጣምሮ እንደሚያይ አንስተው፤ ከተሞች የሥልጣኔ መገለጫ እንዲሆኑ፣ ያላቸውን ፀጋዎች በመለየትና በማልማት፣ የሰውን አቅም ከተፈጥሮና ከኢኮኖሚያዊ ሀብቶች ጋር በማቀናጀት ለጋራ ብልፅግና መሥራትን እንደሚጠይቅ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በከተማችን የልማት ጉዞ እስካሁን የተጓዝነው ርቀት ጠንካራ መሠረት የጣለ ቢሆንም የሚቀረን ረጅም ጉዞ እንዳለ እናውቃለን ብለዋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያም ለዘመናት ከተጫኗት ድህነትና ልዩ ልዩ ችግሮች በዘላቂነት ለመላቀቅ፣ ቀጣይነት ያለው ለውጥ ለማምጣትና ወደ ብልፅግና ለመሸጋገር የጀመረችው ጉዞ ፍሬ እያፈራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ሆኖም ይህንን እልህ አስጨራሽ ጉዞ ወደ ተሟላና ዘላቂ ለውጥ ለመቀየር የሁሉንም ዜጎች ርብርብ፣ ቁርጠኝነትና ተሳትፎ ያስፈልጋል ያሉ ሲሆን፤ ሁላችንም ለለውጡ በቁርጠኝነት መትጋት ይገባናል ሲሉም አስገንዝበዋል።
ያገኘነውን ዓለም አቀፍ እውቅናም እንደ መዳረሻ ሳይሆን እንደ ተጨማሪ ኃላፊነትና ለበለጠ ሥራ ማበረታቻ እንወስደዋለን ብለዋል።
ይህንን ተነሳሽነት በመያዝ ሁሉም የኢትዮጵያ ከተሞች የሥልጣኔና የብልፅግና መሠረት እንዲሆኑ እንሠራለን። አቅሞቻችንን በመደመር፣ ፀጋዎቻችንን ወደ ተጨባጭ ውጤት በመቀየር፣ ክብራችንን የሚመጥን የብልፅግና ግብ ለመድረስ ትጋታችንን እናጠናክራለን ነው ያሉት።
ከተሞቻችን የመደመር ሥልጣኔ መዳረሻ፣ ለነዋሪዎቻቸው ምቹና ተስማሚ የኑሮ አካባቢ፣ ለቀጣዩ ትውልድም ዘላቂ የብልፅግና ውርስ እንዲሆኑ በጋራ እንሠራለን ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
Exit mobile version