አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ክልል የ2013 ዓመትን ለመቀበል በሚቀሩት አምስት የጳጉሜን
ቀናት “መጪው ዘመን የመተሳሰብና የፍቅር ነው” በሚል ልዩ መሪ ሃሳብ እንደሚያከብር አስታወቀ፡፡
ቀናት “መጪው ዘመን የመተሳሰብና የፍቅር ነው” በሚል ልዩ መሪ ሃሳብ እንደሚያከብር አስታወቀ፡፡
የክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙልነህ መርሃ ግብሩን አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፏል።
አቶ ግዛቸው አዲሱን ዓመት ለመቀበል በሚደረገው ዝግጅት ህዝቡ መጪውን ዘመን በመተባበር እና በአንድነት እንዲሁም የተግባራዊ ለውጥ ውስጥ በመግባት ለውጤታማነት የሚረባረብበት እንዲሆን የንቅናቄ መረሃ ግብር እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል፡፡
በመረሃ ግብሩ መሰረትም አምስቱ ቀናት ጳጉሜን 1 የፍቅርና የመተሳሰብ ቀን ፣ ጳጉሜን 2 የሠላም ቀን፣ ጳጉሜ 3 የወንድማማችነት፣ ጳጉሜን 4 የምስጋና እና ጳጉሜን 5 የአንድነት ቀን ሆነው እንደሚታሰቡ ይፋ አድርገዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ሁሉም ቀናቶች የመተሳሰብ፣ የፍቅር የሠላምና የአንድነት ናቸው ያሉት ሲሆን ሁሉም ሰው በየቀኑ እነዚህን የሰብዓዊነት ልክ የሆኑ ስነ-ባህርያት በመለማመድ ሀገርና ወገንን ለመጥቀም ተግቶ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እየተከላከለ አዲሱን ዓመት በተስፋ እንቀበላለን ያሉት አቶ ግዛቸው አምስቱን የመታሰቢያ ቀናት ምክንያት በማድረግ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የበጎፍቃድ አገልግሎት ስራዎች እንደሚሰሩም ነው ያነሱት፡፡
አቅም ደካሞች በመደገፍ፣ ባለውለታዎቻችን በመጠየቅና በማበረታታት እንዲሁም ደም በመለገስና ከተሞቻችን በማፅዳት ለማሳለፍ ሁሉም የክልሉ ነዋሪዎች ዝግጅት እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በናትናኤል ጥጋቡ

