Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በ2019 የተጠናከረ የኢኮኖሚ እድገት እንደሚኖር ይጠበቃል – ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2019 በጀት ዓመት የኢኮኖሚ አመላካቾች የተጠናከረ የኢኮኖሚ እድገት እንደሚኖር ያመለክታሉ አሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ስምንተኛ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት አካሂዷል፡፡
በዚሁ ወቅት ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እንዳነሱት÷ በሲሚንቶ ምርት፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨትና በብረታብረት ምርቶች ላይ የታዩ መሻሻሎች በአጠቃላይ የኢንዱስትሪ ዘርፉ ንቁ እንቅስቃሴ እንደሚኖረው ይጠቁማሉ፡፡
የአገልግሎት ዘርፍ ዋና ዋና አመላካቾች ማለትም የቱሪስት ፍሰት፣ የአየር ትራንስፖርት፣ የብድር አቅርቦት መሻሻሎች ዘርፉ የበለጠ እንደሚያድግ ማሳያ እንደሆኑ ገልጸዋል።
እንዲሁም የወርቅ ወጪ ንግድ፣ የካፒታልና የጥሬ እቃ ምርቶች ገቢ ንግድ እድገቱን እንደሚያጠናክሩም አብራርተዋል።
መሰረታዊ ገንዘብ በመስከረም ወር 2019 መጨረሻ 87 ነጥብ 2 በመቶ ዓመታዊ እድገትን እንዳስመዘገበ በማንሳት፤ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው 72 ነጥብ 6 በመቶ አንጻር ጭማሪ እንዳሳየ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላላ የገንዘብ አቅርቦት ዓመታዊ እድገት ባለፈው ዓመት ከነበረው 33 ነጥብ 2 በመቶ አሁን ላይ 40 ነጥብ 2 በመቶ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ይህም ከሚጠበቀው የሀገር ውስጥ ምርት አንጻር ከፍተኛ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ከሪፎርሙ በፊት ለጠቅላላ የገንዘብ እድገት የሀገር ውስጥ ብድር ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረው አስታውሰው፤ አሁን የተጣራ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከፍ ያለ ድርሻ እንደያዘ አንስተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ የባንክ ዘርፉ ዝቅተኛ የተበላሸ ብድር መጠንና በቂ ካፒታል ያለው በመሆኑ ጤናማና የተረጋጋ ሆኖ እንደቀጠለ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።
የባንኮች የሩብ ዓመቱ የተቀማጭ ገንዘብ ክምችት 85 ነጥብ 4 በመቶ፤ አጠቃላይ የብድር ክምችት ደግሞ 4 ነጥብ 6 በመቶ ዓመታዊ እድገት ማስመዝገቡን ጠቁመዋል፡፡
የበጀት ፖሊሲ ስርዓት ጥንቃቄ የተሞላበት፣ ከብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ጋር የተጣጣመ እንዲሁም ከአጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው አጀንዳ ጋር የተናበበ እንደነበር አመልክተዋል።
መንግሥት በበጀት ዓመቱ ምንም ብድር ከብሔራዊ ባንክ ስላልወሰደ ያለ ብሔራዊ ባንክ ብድር ቆይታው ከ27 ወራት በላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ይህም የዋጋ ግሽበቱን ለማስተካከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል።
በመልካም ፈቃዱ
Exit mobile version