Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመላው ሀገሪቱ 107 ዘመናዊ ሰው አልባ የአየር ሁኔታ መመዝገቢያ መሳሪያዎችን ልተክል ነው – ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በመላው ሀገሪቱ 107 ዘመናዊ ሰው አልባ የአየር ሁኔታ መመዝገቢያ መሳሪያዎችን ለመትከል ዝግጅቴን አጠናቅቄያለሁ አለ ‎የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ እንስቲትዩት፡፡
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ እንስቲትዩት የ2019 ዓ.ም የበጋ ወቅት የአየር ጠባይ አዝማሚያ ትንበያ ይፋ ማድረጊያ መርሐ ግብር በሚዛን አማን ከተማ እያተካሄደ ነው።
‎
የኢትዮጵያ ሚትሪዎሎጂ እንስቲትዩት ዳይሬክተር እና የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ተወካይ ፈጠነ ተሾመ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ኢንስቲትዩቱ በመላው ሀገሪቱ ባሉ 11 ማዕከላት የአየር ትንበያ እና የአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
‎እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በግብርናው ዘርፍ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ባላቸው ሀገራት‎ የአየር ሁኔታ ትንበያ አገልግሎት ያለው አስፈላጊነት ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሚትሪዎሎጂ እንስቲትዩት ከዚህ ቀደም በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረዥም ጊዜ ሊከሰቱ የሚችሉ የአየር ሁኔታ ትንበያ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ሲያደርስ መቆየቱን ገልጸው ተቋሙ በተለያዩ ዘርፎችም ሰፊ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም ተቋሙ የአየር ትንበያን በዘመናዊ መልኩ ለማከናወን የሚያስችሉ 107 ሰው አልባ መሣሪያዎችን በመላው ሀገሪቱ ለመትከል ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቀዋል።
አዲስ የሚተከሉት መሣሪያዎች በ15 ደቂቃ መረጃን ማድረስ የሚችሉ ሲሆኑ ከዚህ ቀደም አገልግሎት ሲሰጡ ከነበሩ መሣሪያዎች በእጅጉ የተሻሉ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ከፈረንጆቹ 2021 ጀምሮ የዓለም አቀፉን የአየር ጠባይ ማዕቀፍን ተቀብላ ብሔራዊ የአየር ጠባይ ማዕቀፍን በማዘጋጀት በግብርና፣ ውኃ፣ ጤና እና አደጋ ሥጋት ዙሪያ የትንበያ መረጃዎችን በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ሊከሰቱ የሚችሉ የአየር ሁኔታ መረጃዎችን የማድረስ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
‎
ኢንስቲትዩቱ ከቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ጋር በመሆን በቆላማ አካባቢዎች ሊከሰቱ የሚችሉ የአየር ሁኔታና አደጋ ሥጋት ትንበያ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ እያደረሰ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
‎በፍሬው አለማየሁ
Exit mobile version