Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከውጭ ነዳጅ ጥገኝነት ወደ ሀገር ውስጥ ሀብት አጠቃቀም፤ የመደመር መንግሥት የከተማ ልማት አዲስ ምዕራፍ!

በአዲስ አበባ የተጀመረው ከነዳጅ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ የተሸጋገሩ የከተማ አውቶቡሶችን ወደ ሥራ ማስገባት ተራ የትራንስፖርት ለውጥ ብቻ አይደለም።

በመደመር መንግሥት የልማት ዕይታ ውስጥ ሲታይ፣ የሀገርን ሀብት ወደ ሕዝብ ተጨባጭ ጥቅም የመቀየር፣ የኢኮኖሚ ነፃነትን የማጠናከር፣ የቴክኖሎጂ አቅምን የማሳደግና ሰው ተኮር የከተማ ልማትን የማረጋገጥ ስትራቴጂካዊ ርምጃ ነው።

በጥቅምት 22 ቀን 2019 የመጀመሪያዎቹ 26 ከነዳጅ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ የተቀየሩ አውቶቡሶች ወደ አገልግሎት ገብተዋል። 400 ተጨማሪ አዳዲስ የጋዝ አውቶቡሶችም እንደሚመጡ ተገልጿል። ይህ ለውጥ ከሚያመጣቸው የታሪፍ፣ የወጪና የአካባቢ ጥቅሞች ባሻገር ትልቅ የልማት ትርጉም አለው።

በመደመር መንግሥት ዕይታ ለከተማዋና ለሕዝቡ ያለውን ትርጉም ዋና ዋና ነጥቦች ስንመለከት:-

የሀገርን የተፈጥሮ ፀጋዎችን ወደ ሕዝብ ተጨባጭ ጥቅም መቀየር!

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶች ያሏት ሀገር ናት። ነገር ግን የሀብት መኖር ብቻውን ልማት አያመጣም፤ ዋናው ጉዳይ ያለንን ሀብት ወደ ምርታማነትና የሕዝብ ጥቅም መቀየር ነው።

በጎዴ የሚመረተውን የተፈጥሮ ጋዝ ወደ መዲናዋ በማምጣት፣ በከተማ ትራንስፖርት ውስጥ መጠቀም መቻሉ የዚህ ሀሳብ ተግባራዊ ማሳያ ነው።

ይህም ሀገራችን ከተፈጥሮ ፀጋዎቿ ተጠቃሚ ብቻ ሳትሆን፣ ፀጋዎቿን በመጠቀም ለዜጎቿ የተሻለ ኑሮ መፍጠር እንደምትችል ያሳያል።

የውጭ ምንዛሬ ጫናን መቀነስና የኢኮኖሚ ነፃነትን ማጠናከር!

የነዳጅ ግዢ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪ ከሚያስከትሉ ዘርፎች አንዱ ነው። የከተማ አውቶቡሶች በአገር ውስጥ በሚመረት የተፈጥሮ ጋዝ መንቀሳቀሳቸው ከውጭ የሚገባ ነዳጅ ላይ ያለንን ጥገኝነት ለመቀነስ ያግዛል።

ይህም ማለት፦

– ለነዳጅ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ መቆጠብ፤

– የሀገር ውስጥ ሀብትን ለምርታማ ዘርፎች ማዋል፤

– በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መዋዠቅ ምክንያት የሚፈጠርን የኢኮኖሚ ጫና መቋቋም፤

– የሀገርን የኢኮኖሚ መቋቋም አቅም ማጠናከር ማለት ነው።

ይህም እንደ ሀገር የተጀመሩ የራሳችንን ሀብት ተጠቅመን የራሳችንን የኢኮኖሚ ጫና የመቀነስ ጉዞ የሚያጠናክር ነው።

በዜጎች ላይ ሊደርክ የሚችል ተፈጥሮዋዊና ሰው ሰራሽ ጫናዎችን መቀነስ!

የትራንስፖርት ወጪ የከተማ ነዋሪዎችን ዕለታዊ የኑሮ ወጪ ከሚወስኑ ነገሮች አንዱ ነው።

የአውቶቡስ የሥራ ማስኬጃ ወጪ ሲቀንስ ይህ በትክክል ወደ ተጠቃሚው ከተላለፈ፣ ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ የትራንስፖርት አገልግሎት ያገኛሉ።

የከተማ ልማት ማለት መንገድ፣ ሕንፃና ድልድይ መገንባት ብቻ ሳይሆን፣ ሰዎች በንጹህ አየር፣ በጤናማ አካባቢና በተሻለ የኑሮ ሁኔታ እንዲኖሩ ማስቻልም ነው።

ከናፍጣ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ መሸጋገር የተሽከርካሪዎችን የተወሰኑ የአየር ብክለት አመንጪ ጋዞችና ቅንጣቶች ለመቀነስ ያግዛል።

በዚህም፦

– የአየር ብክለትን መቀነስ፤

– ለከተማ ነዋሪዎች ጤናማ አካባቢ መፍጠር፤

– የአረንጓዴ ከተማ ግንባታን ማጠናከር፤ እና

– የከተማን የአካባቢ ዘላቂነት ማሳደግ ማለት ነው።

እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ከናፍጣ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ መሸጋገር ወደ ዘላቂ የኃይል አጠቃቀም የሚወስድ ጠቃሚ የሽግግር እርምጃ ነው።

የሀገር ውስጥ አቅምን፣ ቴክኖሎጂንና እውቀትን ማሳደግ!

ከዚህ ፕሮጀክት ትልቅ ትምህርት የሚገኘው የተፈጥሮ ጋዝን ማምረት ብቻ ሳይሆን ለተግባራዊ ጥቅም ማዋል የሚያስችል ቴክኖሎጂና አቅም መገንባት መቻልን ነው።

ጋዙን ከማምረቻ ቦታው ወደ አዲስ አበባ ማጓጓዝ፣ የጋዝ ማደያዎችን መገንባት፣ አውቶቡሶችን ማስተካከልና በሀገር ውስጥ የሰው ኃይል ሥራውን ማከናወን አዲስ የእውቀትና የቴክኖሎጂ አቅም ይፈጥራል። ይህም በሀገራችን ልጆች ሆኖ ታይቷል፤ ትልቅ ስኬትም ነው።

ይህ በቀጣይ ለሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎችም የሚስፋፋ አቅም ነው። የሀገር ውስጥ ባለሙያዎችን ማብቃት፣ የቴክኒክ እውቀትን ማስፋፋት፣ የጥገናና የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪን ማጠናከር ያስችላል።

የመደመር መንግሥት የልማት ጉዞን በተግባር ማሳየት!

የመደመር ዋና መርህ ያሉንን ሀብቶች፣ አቅሞች፣ እውቀቶችና የልማት እድሎች አቀናጅቶ ለጋራ ዓላማ ማዋል ነው።

ይህ ፕሮጀክትም በዚሁ ዕይታ ሲታይ በተለያዩ ዘርፎች ያሉ አቅሞችን አቀናጅቶ ውጤት የማምጣት ተግባራዊ ማሳያ ነው።

– የኢነርጂ ዘርፍ የሚያመነጨው ሀብት፤

– የትራንስፖርት ዘርፍ የሚያቀርበው አገልግሎት፤

– የቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚያመነጨው መፍትሔ፤

– የሰው ኃይል የሚያበረክተው እውቀት፤

– የመንግሥት ተቋማት የሚያደርጉት ቅንጅት።

እነዚህ ሲዋሃዱ የአንድ ዘርፍ ስኬት ብቻ ሳይሆን የሀገር አጠቃላይ የልማት አቅም ይጠናከራል።

አዲስ አበባን አለም አቀፍ ተወዳዳሪና ዘመናዊና ከተማ ማድረግ!

አዲስ አበባ የሀገሪቱ መዲና ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ ዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ማዕከል ናት። ስለዚህ የከተማዋ የትራንስፖርት ሥርዓት ዘመናዊ፣ ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው፣ ቀልጣፋና አካባቢን የሚጠብቅ መሆን አለበት። ይህንንም ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል።

የተፈጥሮ ጋዝ አውቶቡሶች መግባት ከኤሌክትሪክ አውቶቡሶች፣ ከቀላል ባቡር፣ ከዘመናዊ የአውቶቡስ መስመሮችና ከእግረኛ ተስማሚ የከተማ መሠረተ ልማቶች ጋር በተቀናጀ መልኩ ሲዳብር አዲስ አበባን የተሻለ የኑሮ ሁኔታ ያላት ከተማ እንደሚያደርጋት የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል።

አዲስ አበባን የብልፅግና ማሳያ ከተማ የማድረጉ ሂደት ከዚህም በላይ ጎልቶ ይቀጥላል።

 

Exit mobile version