አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24 ቀን 2019 ዓ.ም (ኤፍ ኤም ሲ) በመዲናዋ የተቀናጀ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ግንባታ የኢትዮጵያን የስፖርት ገጽታ ወደ ላቀ ደረጃ እያሸጋገረ ይገኛል አሉ ስፖርት ዘርፍ አመራሮች።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን በአዲስ አበባ ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችና ስታዲየሞች መገንባታቸው ለአትሌቶች ውጤታማነት እና ታላላቅ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
አክለውም አደይ አበባ ስታዲየም ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ ጠብቆ እየተገነባ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ፕሬዝደንቱ በመዲናዋ የሚከናወኑ ዘርፈ ብዙ የስፖርት መሠረተ ልማቶች ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ወሳኝ አስተዋጽኦ አላቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ጥራቱን የጠበቀ የስፖርት መሠረተ ልማት ዝርጋታ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በባለቤትነት እንድታዘጋጅ የሚያስችላት መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ውሹ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ እያሱ ሰለሞን በበኩላቸው፣ በአዲስ አበባ ከተማ አጠቃላይ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች በከተማ ልማት ተካተው መገንባታቸው በዘርፉ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ችለዋል ብለዋል።
አሁን ላይ የወጣቶችን ፍላጎት የሚመጥኑ የስፖርት ማዘውተሪያዎች በብዛትና በጥራት መገንባታቸው ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮችን መቅረፍ መቻሉንም ተናግረዋል።

