አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24 ቀን 2019 ዓ.ም (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገር ነፃነት፣ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ክብር የሚጠበቀው ለሀገራቸው ደኅንነት የሚታገሉና ለሕልውናዋ ዋጋ የሚከፍሉ ዜጎች ባላቸው ጽናት ነው።
ኢትዮጵያ በረጅም የታሪክ ሂደቷ ነፃነቷንና ሉዓላዊነቷን ጠብቃ የዘለቀችውም ብሔራዊ ጥቅምን ከግል ፍግላጎት ባስቀደሙ የሀገር ጀግኖች መሥዋዕትነት ነው።
ይሁንና ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰሜን ዕዝ ላይ በውስጥ ባንዳዎች የተፈጸመው ጥቃት ከባድ የሀገር ቁስል ሆኖ ተመዝግቧል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈጸመው ይህ ድርጊት የሠራዊቱን ደህንነት ከመጉዳት ባለፈ፣ በዜጎች መካከል የነበረውን መተማመን ለማዳከምና ሀገሪቱን ወደ ከፋ የግጭት ቀጠና ለመቀየር የተከፈተ አደገኛ ምዕራፍ ነበር።
የሰሜን ዕዝ ሠራዊት የኢትዮጵያን ድንበርና የሕዝቧን ደህንነት ለመጠበቅ የቆመ አለኝታ ለዓመታት በአስቸጋሪ የጦር ሜዳዎች ተሰማርቶ ሀገርን ሲያገለግል የኖረ ሠራዊት እንደመሆኑ በወቅቱ የደረሰበት ጥቃት በወታደራዊ ታሪክ የማይረሳ አሳዛኝ ክስተት ሆኗል።
ይህም የሀገር ተቋማትን የማፍረስና የብሔራዊ አንድነትን መሠረት የማናጋት ሴራ የተጠነሰሰበት ሰራዊቱ ለሀገሩ የሚከፍለው የመስዕዋትነት ጥግም የታየበት ነበር፡፡
በህገወጡ ህወሀት የተፈጸመው ያ አስከፊ ድርጊት የመከላከያ ሰራዊቱን አቅም በማዳከም በሀገር ሉዓላዊነትና ሰላም በዜጎች ደህንነትና በብሔራዊ አንድነት ላይ ከባድ ቀውስ ለማስከተል ያለመ ነበር፡፡
የህዝብ መተማመንን እና የጋራ ልማት ጉዞን ለማደናቀፍ የተሰነዘረው የግፍ ጥቃት በተቃራኒው የሀገሪቱን ሕልውና የሚፈትኑ ከባድ ሁኔታዎች ኢትዮጵያን እና የህዝቧን የመቋቋም አቅም ከማዳከም ይልቅ በቁጭት ለአንድ አላማ አስተባበረ።
የመከላከያ ሠራዊቱ ከደረሰበት ከባድ ፈተና ራሱን እንደገና በማደራጀት የሀገርን ሕልውና እና ደህንነት ለመጠበቅ የሚያስችለውን ተልዕኮ ለመወጣት በቆራጥነት ተነሳ። ይህ ሂደት የመከላከያ ሠራዊቱን ተቋማዊ ጽናት፣ ሙያዊ ዝግጁነትና ሀገራዊ ኃላፊነት የሚያሳይ ነው።
ይህ የታሪክ ጠባሳ የሀገር አንድነትን ማጠናከር፣ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት፣ የሕግን የበላይነት ማክበርና በጋራ የሀገር ጥቅም ዙሪያ መሰባሰብ የሁሉም ዜጎችና ተቋማት የጋራ ግዴታ መሆኑን እንዲሁም በሀገር ላይ የሚደርሱ ፈተናዎችን መከላከል የመከላከያ ሠራዊት ብቻውን የሚወጣው ኃላፊነት አለመሆኑን ያስገነዘበ ነው።
ለሀገር ነፃነትና ክብር በተደረገው ትግል የተከፈለው መሥዋዕትነት ለትውልድ የሚያስተላልፍ ታሪክ ነው። ለሀገር ደኅንነትና ሉዓላዊነት ሕይወታቸውን የሰጡ
የሰራዊቱን አባላት መዘከር መሥዕዋትነታቸውን ማስታወስ ብቻ ሳይሆን፣ የሰላምን፣ የአንድነትንና የተቋማዊ ጥንካሬን ዋጋ መረዳትም ነው።
ጥቅምት 24 አንድነትን በማጠናከር፣ ተመሳሳይ ታሪክ ዳግም እንዳይከሰት በሀገር ፍቅር ስሜት ለጋራ አላማ የሚያሳስብ ቀን ነው።
በምሕረት ደምሴ

