Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

እንዳይደገም ሁሌም እንዘክራለን!

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ታሪክ የሚያስተምረን ከድልና ከስኬት ብቻ አይደለም፤ ከውድቀት፣ ከክህደትና ከታላላቅ ፈተናዎችም ጭምር ነው።
አንዳንድ ክስተቶች በታሪክ ውስጥ እንደ ድል ቀን ይመዘገባሉ፤ ሌሎች ግን በሕዝብ ልብ ውስጥ የማይጠፋ ጠባሳ በማሳረፍ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይሸጋገራሉ፡፡ ጥቅምት 24ም ከእነዚህ የማይረሱ ታሪካዊ ክስተቶች አንዱ ነው።
ይህ ዕለት በኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈጸመውን ከባድ ጥቃት ከማስታወስ ባለፈ፣ የሀገር ደኅንነትን፣ የብሔራዊ አንድነትንና የሰላም ዋጋን ዳግም እንድናስብ የሚያደርግ ታላቅ ትምህርት ይዟል።
በዚያ ዕለት ሀገርን ከውጭ ጠላት ለመጠበቅ በተጠንቀቅ የቆመው የመከላከያ ሰራዊት ወገን ነው በሚለው በውስጣዊ ክህደት የተሞላ አስከፊ ጥቃት ደረሰበት።
በሰራዊቱ ላይ የተፈጸመው ይህ ድርጊት በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ የጥቁር ምዕራፍ ሆኖ ተመዝግቧል። ለሀገር ሉዓላዊነትና ደኅንነት በታማኝነት የቆመ ተቋም ከውስጥ በክህደት መጠቃቱ የሰራዊቱን አባላት ብቻ ሳይሆን የመላውን ኢትዮጵያዊ ሕሊና የነካ ክስተት ነበር።
ለረጅም ዓመታት በትግራይ ክልል የቆየው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሀገርን ድንበር ከመጠበቅ ባለፈ የክልሉን ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት በመጠበቅ ተግባር ላይ ቆይቶ ነበር። ከሕዝቡ ጋር በአብሮነት የኖረ፣ ደስታውንና ችግሩን የተጋራ፣ በተለያዩ ወቅቶችም ለማኅበራዊ ድጋፍ የተሰማራ ሰራዊት እንደመሆኑ የደረሰውን ክህደት ይበልጥ አሳዛኝ ያደርገዋል።
የዚህ ዕለት ክፉ ክስተት የሰራዊቱን አባላት ሕይወትና ሰብዓዊ ክብር የነካ ከባድ ጉዳት ከማድረሱም በላይ በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ላይ ጥልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል።
እንደዚህ ያሉ ታሪካዊ ክስተቶችን ማስታወስ ጥላቻን ለማቆየት ሳይሆን የክህደትን ዋጋ፣ የሰላምን አስፈላጊነትና የተቋማትን የታማኝነት መሠረት ለመረዳት ነው። ትውስታው ለሰማዕታት ክብር ለመስጠት፣ መሰል አሳዛኝ ክስተቶች ወደፊት እንዳይደገሙ ለመሥራት በሚያነሳሳም መልኩ ነው።
የጥቅምት 24 ትውስታ ለሰራዊቱ የሀዘን ቀን ብቻ አይደለም፤ ተቋማዊ ጽናትን ይበልጥ የሚያጠነክርና የዝግጁነትን አስፈላጊነት የሚያስገነዝብ ትምህርት እንጂ።
በዚህ መርህ መሠረት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በታሪክ ካጋጠሙት ፈተናዎች ትምህርትን በመውሰድ በሰው ኃይል፣ በትጥቅና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም የበለጠ ብቁ የሆነ ተቋም ገንብቷል፡፡
ይህ ዕለት ዛሬ ሲዘከር፤ ያለፈው ጥቅምት 24 የተፈጠረው ክስተት ዳግም እንደማይፈጠር እርግጠኛ የሆነ፤ ዓለም የደረሰበት የሰው ሀይል ብቃትን ከዘመናዊ ትጥቆች ጋር ባለቤት የሆነ ሰራዊት ተገንብቶ ነው፡፡
ዛሬ ላይ የትኛውም የውጭም ሆነ የውስጥ የጥፋት ኃይል የኢትዮጵያን ሰላም፣ አንድነትና ሉዓላዊነት ለመንካት ቢሞክር፣ የሰራዊቱ የማይበገርና ድል የሚያደርግ አስተማማኝ ክንድ ይጠብቀዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊቱ ሀገርን ለማጽናት የከፈለው ውድ መስዋዕትነት በኢትዮጵያ ህዝብ ልብ ውስጥ ሁሌም በከፍተኛ ክብር ይታወሳል።
ሲታወስ ግን ላይደገም ነው፤ እንዳይደገም ሁሌም እንዘክራለን! የነገዋን ጽኑ፣ ሰላማዊ፣ የተከበረችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጉዞ ውስጥ ሰራዊቱ እንደ ሁሌው ጽኑ ደጀንነቱን አስጠብቆ ይቀጥላል።
በመልካም ፈቃዱ
Exit mobile version