Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የትግራይ ቴሌቪዥን ወደ ሥርጭት ተመለሰ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ቴሌቪዥን ከተቋረጠበት ሥርጭት ወደ አገልግሎት ተመልሷል።
በትግራይ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ ሲሰጥ የነበረው የብሮድካስት አገልግሎት፣ የጦርነትና የጥፋት ተልዕኮ ማስፈጸሚያ ሆኖ በማገልገሉ ምክንያት ፈቃዱ መታገዱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 1238/2013 በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት ባደረገው ክትትልና ቁጥጥር፣ የትግራይ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ የመገናኛ ብዙኃን አዋጁን የሚቃረኑ፣ ብሔራዊ ጥቅምን የሚጻረሩ፣ ጽንፈኝነትን የሚያበረታቱና የሀገርንና የሕዝብን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ይዘቶችን ሲያሠራጭ በመገኘቱ ፈቃዱ መታገዱ ይታወሳል።
የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር ተቋሙ ለክልሉ ሰላምና መረጋጋት አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክትና የሕዝብ ድምፅ እንዲሆን በማሰብ፣ በ“ትግራይ ሚዲያ ኮርፖሬሽን” በሚል አዲስ ስያሜ ፈቃድ ወደ አገልግሎት እንዲገባ አድርጓል።
በዚህ መሠረት አዲሱ ተቋም የብሮድካስት ፈቃድ በማግኘት በዛሬው ዕለት ወደ ሥርጭት ተመልሷል።
የትግራይ ቴሌቪዥን ወደ ሥርጭት መመለሱ፣ በክልሉ የሚዲያ አገልግሎት እንደገና እንዲቀጥል ዕድል የሚፈጥር ሲሆን፣ በአዲሱ ስያሜና የሥራ አቅጣጫ የሕዝብን ድምፅ በማሰማት፣ ለሰላምና ለመረጋጋት የሚያግዙ ይዘቶችን በማቅረብ ሥራውን እንዲያከናውን ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቀደም ሲል ታግዶ የነበረውን “የትግራይ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ” የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ “የትግራይ ሚዲያ ኮርፖሬሽን” በሚል አዲስ ስያሜ ማደሱ ይታወሳል።
ባለሥልጣኑ ለተቋሙ አዲስ የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ የሰጠ መሆኑን እያሳወቀ፣ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ለሚዲያ ኮርፖሬሽኑ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረቡም አይዘነጋም።
በግዛቸው ግርማዬ
Exit mobile version