Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ ከዓለም የቀደመችበት የአረንጓዴ ልማት በብሉምበርግ እይታ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባትና የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ በምታደርገው ጥረት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽግግርን በማጠናከር ላይ ትገኛለች።

በአፍሪካ ከሚገኙ ተሽከርካሪዎች ብዙሃኑ ያረጁና በነዳጅ የሚሰሩ በመሆናቸው የነዳጅ ወጪን ጨምሮ በአህጉሪቱ ኢኮኖሚና የአየር ንብረት ተጽዕኖን የመቋቋም ጥረት ላይ ጫና እያሳደረ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን ጫና በመገንዘብ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ፖሊሲ ጭምር ቀርጻ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በብዛት ለመጠቀም ማበረታቻዎችን እያደረገች ትገኛለች፡፡

ታዋቂው ዓለም አቀፍ ሚዲያ ብሉምበርግ በኢትዮጵያ እየተከናወነ የሚገኘውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ፈጣን ሽግግር የሚዳስስ ልዩ ዘገባ አቅርቧል፡፡

ብሉምበርግ በዚህ ዘገባው ኢትዮጵያ ለሌሎችም ሀገራት አብነት የሚሆን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ጉዞ ላይ መሆኗን አስነብቧል፡፡

በተለይም የአውሮፓ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም በሚል ከሁለት አስርት አመታት በላይ የተለያዩ እቅዶችን ሲያዘጋጁ ቢቆዩም ወደ ተግባር መግባት እንዳልቻሉ ዘገባው አመልክቷል፡፡

ኢትዮጵያ ግን ከንግግር ባለፈ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለይም በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ዘርፍ ባደረገችው ፈጣን ሽግግር ከተቀረው ዓለም ቀዳሚ ሆና መገኘቷን አንስቷል፡፡

ይህ ተግባራዊ ርምጃ የአየር ንብረት ለውጥን ተጽዕኖን ከመቋቋም ባሻገር በሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ሽግግርን በማገዝ ኢኮኖሚያዊ አበርክቶው ከፍ ያለ መሆኑንም አስረድቷል፡፡

በፈረንጆቹ 2033 በኢትዮጵያ የሚገኙ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር 500 ሺህ ለማድረስ እየተሰራ ሲሆን፤ በዚሁ ጊዜ ውስጥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ኃይል መሙያ ጣቢያዎችን 2 ሺህ ለማድረስ መታቀዱንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

ይህ የአረንጓዴ ልማት ውጥን ኢትዮጵያ በየአመቱ ለነዳጅ የምታወጣውን 5 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ወጪ በማስቀረት የእዳ ጫናን በማቃለል ኢኮኖሚዋን በእጅጉ የሚደግፍ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡

በተጨማሪም የልማት ስትራቴጂው ተሽከርካሪዎችን በሀገር ውስጥ በመገጣጠም የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማነቃቃትና የእውቀት ሽግግርን ለማጠናከር የሚያግዝ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የፓሪስ ስምምነትን በሶስት ሥራዎች እየተገበረች ትገኛለች።

ከእነዚህ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ተግባራት መካከል የኤሌትሪክ ተሽከርካሪዎች የቀረቡባቸው ዘላቂ የከተማ ልማት ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል የምታመነጨው ከውሃ ሀብቷ በመሆኑ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ጉዞዋ በጠንካራ የታዳሽ ኃይል አቅም የተደገፈ ነው፡፡

ይህም አስተማማኝና ወጪ ቆጣቢ ኃይል በማቅረብ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽግግር መሰረት የሚጥል እንደሆነም ተመላክቷል፡፡

በዚህ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ሽግግር ሂደት በተለይም ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል አቅርቦት መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ረገድ የተጀመሩ ስራዎችን ይበልጥ ማጠናከር ይጠበቅባታል፡፡

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባትሪዎችን የሚያቀርበው ዶዳይ ኩባንያ መስራች የሆኑት ዩማ ሳሳኪ እንደሚሉት፥ ኩባንያቸው በኤሌክትሪክ ለሚሰሩ ሞተር ሳይክሎች የባትሪ መለዋወጥ ቴክኖሎጂን በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል፡፡

ይህ ቴክኖሎጂ ባትሪዎችን ቻርጅ ለማድረግ የሚወስደውን ጊዜ ከመቆጠብ በተጨማሪ የባትሪ ቻርጅ ማድረጊያ መሰረተ ልማት ውስንነትን ለመቅረፍ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ንፁህ፣ ቀልጣፋና ዘላቂ የትራንስፖርት ሥርዓት የምታደርገውን ሽግግር ለማረጋገጥ መሰል ፈጠራዎችን ማጠናከር ይገባል፡፡

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በኃይለማርያም ተገኝ

Exit mobile version