አዲስ አበባ ጥቅምት 25፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ጋር በመቀናጀት የኢትዮጵያን አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) ከ2019 ዓ.ም ጀምሮ መለካት የሚያስችል አዲስ ስሌት በዛሬው ዕለት ይፋ ተደርጓል።
የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር አቶ በረከት ፍስሃጽዮን እንዳሉት፤ የቀድሞው የኢኮኖሚ መለኪያ አዳዲስ የኢኮኖሚ መረጃዎች ያልተካተቱበት እንዲሁም አዲስ የኢኮኖሚ ቅርፅ በአሮጌ መለኪያ ሲለካ የቆየበት ነው ብለዋል።
አዲሱ ስሌት በቅርቡ የተካሄዱ መረጃዎች የተካተተበት ወቅታዊ የሆነ የኢኮኖሚ ሁኔታን የሚያመለክት መሆኑን ገልጸው በአዲሱ ስሌት የኢትዮጵያ የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት 210 ቢሊየን ዶላር እንደሆነ አመልክተዋል።
ስሌቱ የኢትዮጵያን አሁናዊ የኢኮኖሚ ሁኔታን የሚያመላክት፣ ለፖሊሲና ዕቅድ ትክክለኛ ግብዓት በመሆን እንዲሁም ከአጋር አካላት ጋር የምታደርገውን ድርድር አቅም ከፍ የማድረግ ጠቀሜታ እንዳለው አመላክተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ይህ ታላቅ ሥራ በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች የተሰራ በመሆኑ የስታስቲክ ሉዓላዊነት መረጋገጥያስቻለ መሆንን ተናግረዋል።
መረጃው በዓለም አቀፍ ተነፃፃሪና ተአማኒ እንዲሆን ተደርጎ የተሰራ መሆኑን በማንሳት ይህ የተሻሻለ ማዕቀፍ ለፊሲካልና ለገንዘብ ፖሊሲ፣ ለሀገር ውስጥ ሀብት ማሰባሰብ አጋዥ እንደሚሆንም አብራርተዋል።
ጠቅላላ ሀገራዊ ምርት አንድ ሀገር በተወሰነ ጊዜ፣ በአብዛኛው በአንድ ዓመት በሀገር ውስጥ ያመረታቸውን ሁሉንም የመጨረሻ ሸቀጦች እና አገልግሎቶች በገበያ ዋጋ የሚለካ ኢኮኖሚያዊ መለኪያ ነው።
በዚህ መለኪያ ውስጥ የቤተሰቦች ፍጆታ፣ የንግድ ተቋማት እና የግል ባለሀብቶች ኢንቨስትመንት፣ የመንግሥት ወጪ እንዲሁም ከወጪ ንግድ የሚገኘው የተጣራ ውጤት ተደምረው የሚሰሉ ሲሆን ኢትዮጵያም ከፈረንጆቹ 1960 ጀምሮ የጠቅላላ ሀገራዊ ምርት መረጃዋን በይፋ ስታሳውቅ ቆይታለች።
ሆኖም እስካሁን ሥራ ላይ የነበረው የ2008 ዓ.ም የመነሻ ዓመት ስሌት በኢኮኖሚው የተፈጠሩ አዳዲስ ለውጦችን እና የዘርፎችን መስፋፋት በበቂ ሁኔታ የሚያንፀባርቁ አለመሆናቸው በመድረኩ ተጠቁሟል።
በዙፋን አምባቸው

