Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ልማት መሪነቷን አጠናክራ ቀጥላለች – ፍራንስ-24

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ለታዳሽ ኃይል ልማት የሰጠችው ትኩረት በተለይም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ያላትን ቁርጠኝነት ከማረጋገጥ ባሻገር ኢኮኖሚዋን እየደገፈ ይገኛል፡፡

በዚህ ረገድ ያከናወነቻቸው ተከታታይነት ያላቸው ተግባራት በታዳሽ ኃይል ልማት ዘርፍ በአፍሪካ ያላትን የመሪነት ሚና ያጠናከረ መሆኑን ፍራንስ-24 ባወጣው ዘገባ አመልክቷል፡፡

ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሀገራት ዋነኛዋ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢ ሀገር መሆኗን የጠቀሰው ዘገባው፤ የንጹህ ኃይል ልማትን በማሳደግ ይህንን ሚናዋን ለማጽናት በፈጣን ሂደት ላይ ትገኛለች ብሏል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ 16 ያህል የውሃ ኃይል ማመንጫዎች ከሀገሪቱ አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ኃይል 95 በመቶ ያህሉን እንደሚያመርቱ በዘገባው ተመላክቷል፡፡

እነዚህ የኃይል መሰረተ ልማቶች የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል ሽፋን ከማሳደግ ባሻገር ለጎረቤት ሀገራት ዘላቂ የኃይል አቅርቦት ሚናዋን እንደሚያጠናክር አስረድቷል፡፡

የኢንዱስትሪ ዘርፍ ባለሙያዎች እንደሚሉት በተለይም እያደገ ከመጣው የኢንዱስትሪ ዘርፉ ፍላጎት ጋር በተጣጣመ መልኩ የኃይል አቅርቦትን ይበልጥ ለማሳደግ የተጀመሩ የኃይል መሰረተ ልማት ሥራዎችን ማጠናከር ይገባል ማለታቸውንም ዘገባው ጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ የካርቦን ልቀት መጠን ከዓለም አማካይ መጠን በ97 በመቶ ዝቅ ያለ መሆኑን በመግለጽ፤ ይህም ለታዳሽ ኃይል ልማት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን አትቷል፡፡

የፈረንሳዩ የዜና አውታር የልማት ሥራዎች ከዋና የኃይል ማዕከላት በተዘረጉ መስመሮች በቀጥታ ኃይል እንደሚያገኙ በተለያዩ አካባቢዎች ባደረገው ቅኝት መመልከቱን ዘግቧል፡፡

በተለይም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ውኃን ቆጥቦ ለኃይል ማመንጫነት ለመጠቀም ያለመ መሆኑንም ነው ዘገባው ያመለከተው፡፡

ኢትዮጵያ የኮፕ 32 ጉባኤን ለማስተናገድ መመረጧን ያስታወሰው ዘገባው፤ ይህም ሀገሪቱ ለታዳሽ ኃይል ልማትና ዝቅተኛ የካርቦን ልቀትን የሚጠቀም እድገትን እውን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን ለዓለም የምታሳይበት ምቹ አጋጣሚ እንደሚሆንም አመልክቷል፡፡

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በኃይለማርያም ተገኝ

Exit mobile version