Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አዲስ አበባ፡ የአፍሪካ የጋራ ርዕይ፣ የትብብርና የልማት መድረክ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አፍሪካ በጋራ ስትቆም ትጠነክራለች፤ በጋራ ስትሠራ ታድጋለች፤ በጋራ ስትወስን የወደፊት ዕጣ ፈንታዋን ትቀርፃለች።
አዲስ አበባ የአፍሪካ የጋራ ቤት ብትሆንም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አህጉራዊ መድረኮች በብዛት የሚስተናገዱባት አልነበረችም። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የከተማዋ መሰረተ ልማቶች እጥረትና አለመዘመን ብሎም ምቹ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ያለመፈጠራቸው ነው።
ይህን ጉድለት ለመሙላትና በሁሉም መስክ አዲስ አበባን የስበት ማዕከል ለማድረግ በጥቂት ዓመታት የተሰራው ስራ ዛሬ በርካታ ውጤቶችን እያስመለከተን ይገኛል። በአጭር ጊዜ በከተማዋ የተገነቡ ደረጃቸውን የጠበቁ መሰረተ ልማቶችና የዘመኑ አገልግሎት መስጫዎች ከተማዋን ተመራጭ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል አድርጓታል።
አዲስ አበባ አሁን በመቶዎች ብቻ ሳይሆን በአስር ሺዎች ተሳታፊ የሚገኙባቸውን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎች ለማስተናገድ የሚያስችል አስተማማኝ አቅም ፈጥራለች፤ ስብሰባዎቹንም እያስተናገደች ትገኛለች። በዚህ ሳምንትም አንድ ወሳኝ አህጉራዊ ጉባኤ በከተማዋ ይስተናገዳል።
ይሄውም የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ “ለዕድገት መምራት፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ የወደፊት እጣ ፈንታ ቀያሾች ሆነው(Governing for Growth: Political Parties as Architects of Africa’s Economic Future)” በሚል መሪ ቃል በመዲናችን ከጥቅምት 26 እስከ 28/2019 የአፍሪካውያን የድል ምሳሌ በሆነው በታሪካዊው የአድዋ ድል መታሰብያ ሙዚየም ይካሄዳል።
ይህም የሚያሳየው አዲስ አበባ የተለያዩ ሀሳቦች፣ አመለካከቶችና ልምዶች በአንድነት የሚገናኙባት፤ ለአፍሪካና ለዓለም የጋራ መፍትሔዎች የሚፈለጉባት የሰላምና የውይይት ከተማ መሆኗን እንደሚያሳይ ከከንቲባ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
አዲስ አበባም የአፍሪካ አንድነትና የጋራ ዕጣ ፈንታ መለያ ከተማ እንደመሆኗ፣ የአፍሪካ ሕዝቦች በሰላም፣ በትብብርና በጋራ ብልፅግና የሚገናኙባት የዲፕሎማሲና የውይይት ማዕከልነቷን ታጠናክራለች።
አዲስ አበባ የአፍሪካ የጋራ ራዕይ መገናኛ፤ የአፍሪካ ትብብር የጋራ ጥንካሬ፤ የአፍሪካ ብልፅግና የጋራ ግብ መሆኗ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
Exit mobile version