Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የግብፅ እና የሱዳን “2+2”

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ግብፅ እና የሱዳን “2+2” እሚሉት አንድ የጋራ የውይይት መድረክ አላቸው፤ የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የውሃ (መስኖ) ሚኒስትሮች በጋራ የሚሳተፉበት ‘’የዲፕሎማሲ እና የቴክኒክ’’ ስብሰባ ነው።
የጄነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ወታደራዊ አገዛዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ማሂ ኤል ዲን ሳሌም በዚህ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ የመልማት መብት በተፃረረ ሁኔታ “የግብፅን የውሃ መብት ከግብፆች ቀድመን እኛ እንጠብቃለን” ማለታቸው የሱዳን ባለሥልጣናት ሱዳንን ምን ያህል ለግብጽ ተላላኪ ለማድረግ እንደሚሠሩ የሚያሳብቅ ነው።
የሱዳን ወታደራዊ አገዛዝ ከሁሉም በላይ የራሱን ሕዝብ ከጦርነትና ሰብዓዊ ቀውስ መታደግ ሲገባው፤ ዛሬም ጊዜ ያለፈባቸውን እና ፍትሃዊነት የጎደላቸውን የ1929 እና የ1959 ስምምነቶች በመጥቀስ የኢትዮጵያን ጥቅም በሚጎዳ መልኩ ‘’ግብጽን አስቀድሜ እታደጋታለሁ’’ ማለቱ፣ ግብፅም ‘’የሱዳንን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ እና የውሃ መብቷን ለማስከበር አስፈላጊውን ርምጃ ሁሉ ለመውሰድ ዝግጁቷን መግለጿ፣ የሁለቱን ሀገሮች ሕዝቦች የሚጎዳ እንጂ የሚጠቅም አይደለም።
በርግጥ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር “የግብፅን ውሃ ከእነሱ ቀድመን እንጠብቃለን” ማለታቸው፣ ሱዳን አሁን ባለችበት የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በግብፅ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና ሥር ሙሉ በሙሉ መውደቋን በግልጽ ያሳያል።
“2+2” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ የግብጽ እና የሱዳን የምምክር መድረክ ከእያንዳንዱ ሀገር ሁለት ሚኒስትሮች (ማለትም 2 ከውጭ ጉዳይ + ሁለት ከውሃ) በድምሩ አራት ባለስልጣናት የሚገናኙበት ስብሰባ ነው።
ዋና ዓላማውም ‘’የናይል ውሃ የጋራ ደህንነትን መጠበቅ ‘’ በሚል ሽፋን የሕዳሴ ግድብን እና ሌሎች የተፋሰሱን ወንዞች አጠቃቀምና አስተዳደር እኛ መጠቀም አለብን ከሚል የሚመነጭ ነው።
በካይሮ ከተማ ባካሄዱት ሦስተኛው ዙር ስብሰባ መጨረሻ ላይ ያወጡት የጋራ መግለጫም ከቃላት ጋጋታ የተለየ አይደለም።
መግለጫቸው ሁለቱ ሀገራት ጊዜ ያለፈባቸው የቅኝ ግዛት ስምምነቶች እና አሮጌው አካሄድ ዛሬም በውርስ መልክ እንዲቀጥሉ የሚሹ መሆናቸውን ነው የሚገልጸው።
የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ እና የሱዳኑ ማሂ ኤል-ዲን ሳሌም ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ በምሥራቅ የዓባይ ተፋሰስ ላይ የሚደረጉ ማናቸውም ዓይነት የአንድ ወገን ርምጃዎችን በጥብቅ እንቃወማለን ብለዋል በድጋሚ። የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሰ ነው ነገሩ።
ኢትዮጵያ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ የምትመራበት መንገድ ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ ነውም ይላሉ በጋራ መግለጫቸው።
በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት አንድ ሀገር ያልፈረመችበትና ድርድር ላይ ያልተሳተፈችበት ስምምነት በዚያች ሀገር ላይ በእስገዳጅ ሁኔታ ተፈፃሚነት ሊኖረው አይችልም።
ኢትዮጵያ በ1929 እና 1959 የዓባይ ውሃ ስምምነቶች ላይ አልተሳተፈችም፣ አልፈረመችምም። ስለዚህ እነዚህ ስምምነቶች በኢትዮጵያ ላይ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ውጤት ስለሌላቸው ዋጋ ቢስ ናቸው፡፡
የሕዳሴ ግድብ የሁሉንም ወገን ጥቅም የሚጠብቅ፣ ለሱዳንም ቢሆን የጎርፍ አደጋን ከመከላከል በተጨማሪ የግድቡ መሰራት የውሃ ፍሰቱን ስላስተካከለው ለግብርና ሥራቸው ከዚህ ቀደም ያላገኙትን የተለያየ ጥቅም እያሰገኘላቸው እንደሆነ የሱዳን ገበሬዎች ጭምር የሚመሰክሩት ሐቅ ነው።
ኢትዮጵያ የየትኛውንም አካል ፈቃድ ወይም ችሮታ ሳትሻ በራሷ ልጆች ጉልበት፣ ላብ፣ ገንዘብ እና መስዋዕትነት ታላቁን የሕዳሴ ግድብ መገንባት የቻለች ሀገር ናት።
በቀጣይም ኢትዮጵያ እንደ ዓባይ፣ ተከዜ፣ ባሮ አኮቦ እና ኦሞ የመሳሰሉ ወንዞቿን በመገደብና በማልማት ለዘመናት በተፈጥሮ ሀብታቸው እንዳይጠቀሙ የተደረጉ ዜጎቿን ከድህነትና ከጨለማ ለማውጣት የምታደርገውን የብልጽግና ጉዞ በጽናት ትቀጥላለች።
በአጠቃላይ የሕዳሴ ግድብን ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልክ ያጠናቀቀው የመደመር መንግሥት በቀጣይም የኢትዮጵያን ውሃ ሀብቶች በማልማት የሕዝቦቹን ህይወት በመቀየር ታሪካዊ ኃላፊነቱን ይወጣል።
በአሰፋ አሕመድ
Exit mobile version