አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሱዳን ውስጥ በተነሳው ግጭት ግብጽ ተጠቃሚ ሆናለች አሉ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)፡፡
ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ሱዳን ትጠቀመው የነበረውን ውሃ በብቸኝት እየተጠቀመች ያለችው ግብጽ የራሷን ጥቅም ብቻ ለማስከበር ግጭት እንዲቀጥል ትሰራለች ብለዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከተገነባ በኋላ በጋ ላይ ሱዳን ከ4 እስከ 5 እጥፍ ውሃ ማግኘት ችላ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በዚህም ያለ ምንም ወጪ የመስኖ እርሻቸውን ማስፋፋት ይችሉ ነበር ነገር ግን አሁን ያሉበት ሁኔታ እሱን ባለመፍቀዱ ውሃው ምንም ሳይነካ በቀጥታ ወደ አስዋን ግድብ እየገባ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት በናይል ዙሪያ ይለሙ የነበሩ የሱዳን የመስኖ ስራዎች መቋረጣቸውን ጠቁመው፤ በዚህም ግብጽ ተጠቃሚ ሆናለች ሲሉ አመልክተዋል፡፡
ሱዳን ትጠቀመው የነበረው ውሃ ምንም ሳይነካ ወደ ግብጽ እየሄደ በመሆኑ ግብጽ ይህን ጥቅሟን ለማስጠበቅ ግጭቶች እንዲቀጥሉ እየሰራች ነው ብለዋል፡፡
ግብጽ የራሷ የሆነ ውሃ የሌላት ሀገር ብትሆንም፤ ብዙ የውሃ መጠን የሚፈልጉ እንደ ሸንኮራ አገዳ እና ሩዝ ያሉ ሰብሎችን በማምረት የውሃ ብክነትን እያባባሰች መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ይህን የውሃ ሀብት ብቻዋን ለመጠቀም ስትል ምንም ታደርጋለች ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በእመቤት ሲሳይ

