Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የትግራይ ወጣት ከጦርነት ትርፍ እንደማይገኝ በመረዳቱ ለሰላም ፊቱን አዙሯል – ብርጋዴር ጄነራል ገብረእግዚአብሔር በየነ (ወዲ አንጥር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ወጣት ከጦርነት ትርፍ እንደማይገኝ በመረዳቱ እና ሰርቶ መቀየር የሚፈልግ በመሆኑ ለሰላም ፊቱን አዙሯል አሉ የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብርጋዴር ጄኔራል ገብረእግዚአብሔር በየነ (ወዲ አንጥር)።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋትና ልማት እንዲሰፍን ለቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ምዝገባ መጀመሩን ተከትሎ ነዋሪዎች ሰላምና ጸጥታን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ህዝቡ በየአካባቢው የራሱን አስተዳዳሪዎች እየመረጠ እንዲሁም የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ተሀድሶ ስልጠና ማዕከል እንዲገቡ እያበረታታ ይገኛል ብለዋል።

ሰላሟ የተረጋገጠ እና የለማች ትግራይን ለመፍጠር የወጣቱ ሚና ከፍተኛ ነው ብለው ወጣቱ ከጦርነት ትርፍ እንደማይገኝ በመረዳቱና ሰርቶ መቀየር የሚፈልግ በመሆኑ ለሰላም ፊቱን አዙሯል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

አክለውም ይህ በባለአደራ አስተዳደሩ እና በተሀድሶ ስልጠናው ላይ ህዝብ የጣለውን እምነት ማሳያ በመሆኑ የተገኘውን ሰላም በመጠቀም በፍጥነት ወደ ልማት መግባት ይጠበቅብናልም ነው ያሉት።

ስልጠናው በክልሉ ትምህርት ጤና ንግድ እንዲሁም ሌሎች ተቋማት አገልግሎት ላይ የተጀመሩ የለውጥ ተግባራትን ለማቀላጠፍ የሚያስችል የአምራች ሀይል ስብስብን የያዘ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ተስፋአለም ይሕደጎ በበኩላቸው የተጀመረው ሥራ ዓለም አቀፍ የDDR አሠራርን በተከተለና አስፈላጊውን መስፈርት ባሟላ መልኩ መከናወኑን ገልጸው በመቀሌው የተሃድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ላይ የሚሳተፉ 5 ሺህ 500 ሰዎች ምዝገባ ዛሬ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

ሥልጠናውን የወሰዱ ተሳታፊዎች የወሰዱትን ስልጠና ተግባራዊ በማድረግ የማሕበረሰቡን ችግር በመፍታት እንዲሁም ሰላምን በማረጋገጥ ረገድ የራሳቸውን ድርሻ እንደሚወጡም አስረድተዋል።

ዩኤንዲፒ ከፕሪቶሪያው ስምምነት መፈረም ጀምሮ ሰላም እንዲሰፍን ሲደግፍ ቆይቷል ያሉት በዩኤንዲፒ የዲዲአር ፕሮግራም በኢትዮጵያ ዳይሬክተር ባሲል ማሲያ በበኩላቸው አሁን በተገኘው ሰላም እና የተሀድሶ ስልጠናው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ህዝቡን ለመደገፍ እና ክልሉን መልሶ ለማቋቋም የሚያደርገውን ጥረት አድንቀዋል።

ዳይሬክተሩ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች እንዲሁም ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች መሳሪቸውን አስቀምጠው ስልጠናውን በመቀላቀል ለበለጸገች ትግራይ እንዲሁም ኢትዮጵያ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪም አቅርበዋል፡፡

በምሕረት ደምሴ

Exit mobile version