አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የወታደራዊ ሳይንስ ሥልጠናው በአካላዊ፣ በአእምሯዊና በተግባር ዝግጁነት ረገድ አዲስ አቅም ያስጨበጠ ነው አሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)።
ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች በሁርሶ ዕጩ መኮንኖች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ሲወስዱ የቆዩትን የወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ ስልጠና አጠናቅቀዋል።
ጌዲዮን ጢሞቲዮስ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፥ ስልጠናው ወታደራዊ ሳይንስን በተግባር ለመረዳት፣ የመከላከያ ሠራዊቱን የሥራ ሂደትና የስልጠና ሥርዓት በቅርበት ለመገንዘብ ያስቻለ ነው።
ኢትዮጵያ አስተማማኝ የመከላከያ አደረጃጀትና አወቃቀር እንድትገነባ የወታደራዊ ሳይንስ ጥበብን ማወቅ አሥፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።
በዚህ ረገድ የወታደራዊ ሳይንስ ስልጠና ለሲቪል አመራሮቹ ስለወታደራዊ አስተሳሰብ፣ስለ መከላከያ ስርዓት፣ ስለ ሃገራዊ ደህንነትና ስለ ስትራቴጂካዊ ውሳኔ አሰጣጥ ያላቸውን ግንዛቤ ለማስፋት ጠቃሚ መሰረት መፍጠሩን ጠቁመዋል።
ከስልጠናው ያገኙት ተሞክሮ የወታደራዊ ሳይንስን ፋይዳ በተግባር ከመረዳት ባለፈ፣ በአመራር ሥራቸው የተሻለ ግንዛቤና ዝግጁነት እንዲኖራቸው የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አመራሮቹ የሃገርን ደህንነት የስጋት ምንጮችንና የብሄራዊ ጥቅም ጉዳዮች በሰፊው እንዲገነዘቡ ያስቻለ ሥልጠና ነው ማለታቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመለክታል።
የተሰጠው የከፍተኛ አመራሮች የወታደራዊ ሳይንስ ስልጠና የተግባቦት ክፍተትን በማጥበብ፣ የጋራ ግንዛቤን በመፍጠር እና የውሳኔ አሰጣጥ አቅምን በማጎልበት፤ ውስብስብ የሃገር ደህንነት ፈተናዎች ሲያጋጥሙ የሃገርን ዘላቂ ጥቅም የሚያስጠብቁ የተቀናጁ ምላሾችን ለመስጠት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

