Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጉባኤው የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአፍሪካ ዘላቂ ልማት የበኩላቸውን እንዲወጡ ትልቅ ፋይዳ አለው – ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአህጉሪቱ ዘላቂ ልማትና የህዝቦች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የበኩላቸውን እንዲወጡ ትልቅ ፋይዳ አለው አሉ የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፡፡

“ዕድገትን መምራት፤ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሐንዲሶች” በሚል መሪ ሃሳብ 2ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።

ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ጉባዔው ፓርቲዎች ለአህጉሪቱ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገት፣ ለልማትና ለዜጎች ኑሮ መሻሻል የላቀ ሚና እንዲወጡ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ጉባዔው ገዥም ሆኑ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገራቸው ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ሽግግር እንዲሁም የልማት ዕድሎች ያላቸውን ሚና በመገንዘብ በትብብር እንዲሰሩ የሚያስችል መድረክ መሆኑን አንስተዋል።

ፓርቲዎች በምርጫ ወቅት ተወዳድሮ መንግሥት ለመመስረት ከሚያደርጉት ፉክክር ባሻገር፣ ድህነትን በመቀነስ፣ የስራ ዕድል በመፍጠርና የዜጎችን ህይወት በመለወጥ ረገድ የጋራ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ነው ያሉት።

ጉባዔው የጋራ የአቋም መግለጫ በማውጣት እንደሚጠቃለል ይጠበቃል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version