አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ከብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ጥቅምት 25 ቀን 2019 ዓ.ም የሀገሪቱን ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ግመታን ወቅታዊ (GDP Rebasing) መደረጉን ይፋ አድርገዋል፡፡
ይህ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ግመታን መሠረተ-ዓመት የማሻሻል እና የመለካት ሥራ፣ በኢኮኖሚው የመለኪያ ሥርዓት ላይ የተደረገ ታሪካዊና ወቅታዊ እርምጃ ነው።
አዲስ ስሌት የኢትዮጵያን ጠቅላላ ሀገራዊ ምርት (GDP) ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ መለካት የሚያስችል መሆኑ በማብሰሪያው ስነስርዓት ላይ ተጠቅሷል፡፡
በአዲሱ ስሌት መሰረት የኢትዮጵያ የ2017 በጀት ዓመት አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት 201.4 ቢሊየን ዶላር የደረሰ ሲሆን በበፊቱ ስሌት 126.5 ቢሊየን ዶላር ብቻ ነበር፡፡
በአዲሱ ምርት ግመታ መነሻ መሰረት በ2018 የተመዘገበው ዕድገት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 210.7 ቢሊየን ዶላር መድረሱንና ይህም ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት 3ኛው ትልቅ ኢኮኖሚ ለመሆን በቅቷል።
ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ግመታን ማሻሻል (GDP Rebasing) ሲባል የሀገር ውስጥ ምርትን ለማስላት ጥቅም ላይ የሚውሉትን የዋጋ፣ የምርት ስብጥር እና የአሰራር መረጃዎችን አዳዲስ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ባካተተ መልኩ ወቅታዊ ማድረግ ማለት ነው።
የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ በዓመታት ውስጥ እያደገ ሲሄድ፣ አዳዲስ ዘርፎች ማለትም በኢትዮጵያ አውድ እንደ ዲጂታል ፋይናንስ፣ ቴሌኮም፣ የማዕድን ማውጣት እና ዘመናዊ አገልግሎቶች ስለተፈጠሩ፣ ከዚህ ቀደም ለማስላት የተጠቀምንበት መነሻ (መሠረተ-ዓመት) መጠቀም የሀገሪቱን ትክክለኛ የኢኮኖሚ መጠንና አቅም ማሳየት አያስችልም።
የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር በረከት ፍስሃጽዮን እንዳሉት፤ የቀድሞው የኢኮኖሚ መለኪያ የዲጂታል የገንዘብ ልውውጦችን፣ እንደ ካፒታል ገበያ፣ የበጋ መስኖ ልማትና የኮሪደር ልማት ያሉ አዳዲስ የኢኮኖሚ ልማት መረጃዎች ያልተካተቱበት፣ አዲስ የኢኮኖሚ ቅርፅ በአሮጌ መለኪያ ሲለካ ቆይቷል፡፡
በአዲሱ ስሌት የተገኘው ጭማሪ ኢትዮጵያ በግልጽ ባልተመዘገቡ አዳዲስ ዘርፎች ያሳየችውን ተጨባጭ መዋቅራዊ ሽግግር መኖሩን ያመላክታል።
ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ግመታን ወቅታዊ ማድረግ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው፡፡ በዋናነት በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ የበጀት፣ የፋይናንስ እና የገንዘብ ፖሊሲ ለመቅረጽ ያስፈልጋል።
ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ግመታ ማሻሻያ፣ የሀገራችንን አሁናዊ የኢኮኖሚ ሁኔታን የሚያመላክት፣ ለፖሊሲና ዕቅድ ትክክለኛ ግብዓት በመሆን እንዲሁም ከአጋር አካላት ጋር የምታደርገውን ድርድር አቅም ከፍ ለማድረግ ያስችላል።
ከዚህ በተጨማሪ የሀገሪቱን ትክክለኛ የገበያ መጠን እና የምርታማነት አቅም ለውጭ እና ሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የጠራ መረጃ በመስጠት የኢንቨስትመንት ፍሰትን ያፋጥናል።
ትክክለኛ ስታቲስቲክስ ለስኬታማ የኢኮኖሚ አስተዳደር መሠረት በመሆኑ፣ ይህ የመረጃ ወቅታዊነት ርምጃ ኢትዮጵያ የጀመረችውን መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር በተሻለ እቅድ ለመምራት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በቴዎድሮስ ሳህለ

