Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጂኦፓርኩ በዩኔስኮ መመዝገቡ ለማህበረሰቡ ተጠቃሚነት ወሳኝ ነው – ባለሙያዎች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ጂኦፓርክ በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ ትምህርትና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ማስመዝገቧ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ያደርጋል አሉ በምዝገባ ሂደቱ የተሳተፉ ባለሙያዎች፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ጂኦፓርክ በፓሪስ በተካሄደው 11ኛው የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ጂኦፓርኮች ካውንስል ስብሰባ ላይ እውቅና አግኝቷል።

ይህን አስመልክቶ የጂኦቱሪዝም ባለሙያው እና ጂኦፓርኩን በማስመዝገቡ ሂደት ግንባር ቀደም ተዋናዮች አንዱ እንቁ ሙሉጌታ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ጂኦፓርክ በዩኔስኮ መመዝገቡ ለአካባቢው ማህበረሰብ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው።

ጂኦፓርክ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር የተጣመረ በመሆኑ ህልውናው በማህበረሰቡ ላይ የተመሰረተ ነው በማለት ገልጸው፤ ማህበረሰቡ በጂኦፓርኩ ውስጥ ያሉትን ሀብቶች በአግባቡ በማስተዳደር እንዲጠቀም ምቹ ሁኔታዎች መፈጠር አለባቸው ብለዋል።

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የብሔራዊ ጂኦፓርክ ተጠሪ እና የሥራ ሂደት ኃላፊ አቶ ብሩክ አሥራት በበኩላቸው፤ ጂኦፓርክን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ከሚያስችሉ 101 መስፈርቶች መካከል የማህበረሰብ ተጠቃሚነት ቅድሚያ እንደሚሰጠው ጠቁመዋል።

በዚህ ረገድ ጂኦፓርኩ ከመመዝገቡ በፊት በጥቃቅን እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ማደራጀትን ጨምሮ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን አስታውሰዋል።

3 ሺህ 152 ኪሎሜትር ስኩዌር በሚሸፍነው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ጂኦፓርክ ውስጥ ያሉ ማህበረሰቦች ምርትና አገልግሎታቸውን እንዲያቀርቡ አማራጭ የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግረግን ጨምሮ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ተናግረዋል።

የጂኦፓርኩ በዩኔስኮ መመዝገቡ በጂኦቱሪዝም ዘርፍ ወደፊት ሰፊ እድል እንደሚፈጥር ገልጸው፤ በ’ኢንተርናሽናል ግሎባል ጂኦፓርክ ኔትወርክ’ አባል በመሆን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

በጂኦቱሪዝም የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት የስራ ዕድል የሚፈጥር የአስጎብኝነት ሥልጠና መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

የጂኦፓርኩ ስኬት የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት፣ ልዩ የጂኦሎጂ ቅርስና የቱሪዝም መስህቦች ለዓለም የሚያስተዋውቅ ከፍተኛ ብሔራዊ ድል መሆኑን ባለሙያዎቹ አብራርተዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ የስምጥ ሸለቆ ጂኦፓርክ 14 ወረዳዎችን የሚሸፍን ሲሆን፤ ታላቁን የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆን እና ጢያ ትክል ድንጋዮችን ጨምሮ 46 ጂኦሳይቶችን በውስጡ ያቀፈ ነው።

ኢትዮጵያ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ የስምጥ ሸለቆ ጂኦፓርክን ጨምሮ 25 የሚሆኑ ስፍራዎች ለጂኦፓርክነት የተለዩ ሲሆን፤ በቀጣይ የአፋርን መልከዓ ምድር ለማስመዝገብ ሥራዎች ተጀምረዋል።

ጂኦፓርክ ማለት ማንኛውንም የጂኦሎጂ፣ የተፈጥሮ፣ የባህል እና ታሪካዊ ሃብቶችን በመንከባከብ፣ ለትውልድ ለማስተላለፍ እንዲሁም በውስጡ ያሉ ማህበረሰቦችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲያጎለብቱ ማድረግን የሚካትት ሀሳብ ነው።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በቴዎድሮስ ሳህለ

 

Exit mobile version